የነዋሪዎቻችንን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በትጋት እየሠራን ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የነዋሪዎቻችንን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በትጋት እየሠራን ነው አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባዋ ዛሬ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተገነባውን የበጎነት መኖሪያ ለአቅመ ደካሞችና ለሀገር ባለውለታዎች አስረክበዋል።
ከንቲባዋ ይህንን አስመልክተው በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ ለእኛ የቤት ልማት ማለት ሕንፃ መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎችን ክብር ማስጠበቅ፣ የኑሮ ጥራትን ማሻሻልና የተሻለ ነገ መገንባት ነው።
ለኑሮ በማይመች ሁኔታ የነበሩ ዜጎች በተሟላ መሠረተ ልማት የታገዘ ምቹ መኖሪያ ቤት በማግኘታቸው የኑሮ ጫናቸው መቀነሱን አንስተዋል፡፡
የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመቅረፍና ለነዋሪዎቻችን ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ምቹና ክብር የተሞላበት ኑሮ ለመፍጠር ጥረታችንን አጠናክረን እንቀጥላለንም ነው ያሉት።
ለዚህ በጎ ተግባር ምላሽ በመስጠት አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነው እንዲህ ያለው አጋርነት የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል የተሻለች ከተማ ለመገንባት እንደሚያግዝ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡