የተሳሰረ ታሪክ ያላቸው ኢትዮጵያና ኬንያ የወደፊት እጣ ፈንታቸውም የተሳሰረ ሊሆን ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ኬንያ የተሳሰረ ታሪክ ያላቸው እንደመሆናቸው መጠን የወደፊት እጣ ፈንታቸውም እንዲሁ የተሳሰረ ሊሆን ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኬንያ ኤልዶሬት በተከበረው የማሹጃ ቀን (የጀግኖች ቀን) ብሔራዊ ክብረ በዓል ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በንግግራቸው ለሀገራቸው ነጻነት ለታገሉና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ታላቅ መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች ያላቸውን ታላቅ ክብር ገልጸዋል።
ጀግኖቹ ላበረከቱት አስተዋጽዖ እና ትተውት ላለፉት አሻራ ላቅ ያለ እውቅና ሰጥተዋል።
የኬንያ የጀግንነት እና የመስዋዕትነት ታሪክ፣ ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመከላከል በአንድነት ከቆሙበት ከኢትዮጵያ የአድዋ ታሪክ ጋር በእጅጉ እንደሚመሳሰል አንስተዋል።
እነዚህ የጋራ ታሪኮች ነጻነት በስጦታ የተገኘ ሳይሆን በጀግንነት፣ በአንድነት እና በመስዋዕትነት የተረጋገጠ መሆኑን የሚያስገነዝቡ ናቸው ብለዋል።
በመደመር መንፈስ ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ሰፊ እድሎችን እና የጋራ ብልጽግናን ለመፍጠር በንጹህ ሀይል፣ በመንገድ ትስስር፣ በቴሌኮሙኒኬሽን እና በንግድ ዘርፎች ያለውን ነባር ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ክብር ለተቸራቸው ጀግኖች ሁሉ ላቅ ያለ አክብሮታቸውን በመግለጽ፣ መልካም የማሹጃ (የጀግኖች) ቀን እንዲሆን ተመኝተዋል።