Fana: At a Speed of Life!

ተፈናቃዮች እንደመያዣነት የህገ ወጡ ህወሓት የፖለቲካ ቁማር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገ ወጡ ህወሓት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ በመያዣነት ሲጠቀም ቆይቷል፡፡

ቡድኑ በሕዝብ ተቃውሞ ያጣውን ስልጣን መልሶ ለማግኘት ለአራተኛ ጊዜ ትንኮሳ ቢፈፅምም እየተወሰደበት በሚገኘው የህግ ማስከበር ዘመቻ የቡድኑ ህልውና እየተዳከመ ይገኛል፡፡

ያለ ጦርነት መኖር የማይችለው ሕገ ወጡ ህወሓት በተለያዩ ጊዜያት ባወጀው ጦርነት እታገለልታለሁ የሚለውን የትግራይ ክልል ህዝብ ለከፋ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ዳርጎታል፡፡

ቡድኑ በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ ራሱን ብቸኛ አማራጭ በማድረግ እና የትግራይ ወጣቶች ተራማጅ ፖለቲካን እንዳይከተሉ ህዝቡን እና ቡድኑን አንድ አድርጎ በመመልከት ፖለቲካዊ ጫናን ሲያደርስ ቆይቷል፡፡

ጎረቤት ክልሎችን እንደ ጠላት በመቁጠር ለበርካታ ዘመናት ማንኛውም ትግራዋይ መልካም ጉርብትና እንዳይኖረው እና ከአጎራባች ህዝቦች ጋር በጥርጣሬ እንዲተያይ ሲያደርግም ቆይቷል፡፡

በተጨማሪም ወጣቶች ተምረው እና ሰርተው ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን እንዲረዱ ከማድረግ ይልቅ ወደ አስገዳጅ ውትድርና በመልመል የአፍላ ወጣቶችን ነፍስ ለእኩይ የፖለቲካ ዓላማው ገብሯል፡፡

ከዚህም በላይ ቡድኑ ‘እታገልለታለሁ’ ለሚለው የትግራይ ህዝብ ግድ እንደሌለው የሚያሳየው ህገ ወጡ ቡድን በጀመረው ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት እንዲመለሱ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኑ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትግርኛ ቋንቋ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ÷ ሕገ ወጡ ህወሓት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ በመያዣነት ሲጠቀም መቆየቱን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ተፈናቃዮችን ለመርዳት ወደ ክልሉ የገባን እህል ከተፈናቃዮች ጉሮሮ እየነጠቀ ለጦር መሣሪያዎች መግዣነት ሲጠቀምበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት የጀመራቸውን የባንክ፣ የቴሌኮምና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶች በማስተጓጎል በሕዝቡ ላይ ዳግም ስቃይ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ቢቢሲ፣ ዲ ደብለው፣ አልጀዚራ፣ ሬውተርስ እና ሲኤንኤንን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በትግራይ ክልል ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን በተደጋጋሚ ዘግበዋል።

የፌዴራል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በመጠለያ ጣቢያዎች በቂ ሰብአዊ ርዳታ ቢያቀርብም ቡድኑ በሚፈፅመው ዝርፊያ እና የአቅርቦት መስተጓጎል ምክንያት ተፈናቃዮችን የመርዳት ጥረትን አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል፡፡

በመሆኑም ይህን ህገ ወጥ ስብስብ ለህዝብ የሚጠቅም ዓላማ የሌለው መሆኑ ግንዛቤ ማግኘቱ ወሳኝ ነገር ነው።

የትግራይ ህዝብ ፍላጎቱ የቡድኑ ህይወት ማራዘሚያ ጦርነትና ቀውስ ሳይሆን ልማትና ሰላም መሆኑን አደባባይ በመውጣት ጭምር አረጋግጧል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.