የማይበገር ጀግና ሠራዊት፡ የሉዓላዊነት ጋሻና የሕዝብ አለኝታ
ጀግና ከራስ ጥቅም ይልቅ የሀገርንና የሕዝብን ሕልውና አስበልጦ የሚቆም፣ በችግር ጊዜ ደግሞ የጽናትና የጋሻነት ምልክት ሆኖ የሚሰለፍ ውድ የሕዝብ ልጅ ነው።
በረጅም የታሪክ ጉዞዋ ብዙ የጀግንነት ገደሎችን ያለፈችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬም ድረስ በነጻነትና በሉዓላዊነት ቆማ እንድትቀጥል ያደረገው ዋናው መሠረት የቁርጥ ቀን ልጇ የሆነው የመከላከያ ሠራዊት ነው።
ይህ የጀግኖች ስብስብ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስጠበቅ በኩል የከፈለውንና እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት በቃላት ብቻ ገልጾ ማጠናቀቅ አይቻልም።
በበረሃው እሳት፣ በደጋው ቁር ሳይበገር የሀገርን ዳርቻ እንደ ብረት አጥር ከብቦ የሚጠብቀው ሠራዊት፣ ለሀገሩ ሰላምና ደህንነት ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት አንድም ቀን ወደኋላ ብሎ አያውቅም።
የውጭ ወራሪዎችንና የተላላኪ ባንዳዎችን እኩይ ዓላማ በማክሸፍ ረገድ ያሳየውና የሚያሳየው ተጋድሎ ለትውልድ የሚሻገር ታላቅ የታሪክ አሻራ ነው።
ከተመሠረተ 119 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ጀግንነቱ በጦር ሜዳ ውሎው ብቻ የሚወሰን አይደለም። በሰላም ጊዜም የሕዝቡ ደስታና ሕመም ተካፋይ በመሆን ፍጹም ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን በተግባር ያስመሰከረ ተቋም ነው።
ይህ ከሕዝብ የተወለደ ሠራዊት በላብና በደሙ ኢትዮጵያውያንን የሚያገለግል፤ በወታደራዊ ደንብ ብቻ ሳይሆን በሰውነት እና በሀገር ፍቅር ስሜት የታነጸ እውነተኛ የሕዝብ አለኝታ ነው።
የትኛውም የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ አደጋ ሲከሰት ፈጥኖ በመድረስ የዜጎችን ሕይወት የሚያድነው ይህ የቁርጥ ቀን ልጅ፣ ከሕዝቡ ጋር ያለው ቁርኝት ምን ያህል የጠነከረና መሠረታዊ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ሕዝብም የሠራዊቱን ጋሻነትና አለኝታነት በሚገባ ተረድቶ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ከጎኑ ከመቆም ወደኋላ ብሎ አያውቅም። ሠራዊቱ በየግንባሩ የሚያስመዘግበውን ድል በመደገፍ አጋርነቱን አረጋግጧል።
ለአብነት በዚህ ሳምንት ብቻ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተካሄዱት ደማቅ የድጋፍ ሰልፎች ሕዝቡ ለሠራዊቱ ያለውን ጥልቅ ፍቅርና አክብሮት በግልጽ ያሳዩ ማረጋገጫዎች ናቸው።ሕዝቡ የሚሰጠው ይህ ያልተቋረጠ ድጋፍ ለሠራዊቱ ዋና የብርታት ምንጭ ነው።
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊታችን የታሪክ ውርስና ሕዝባዊነት መንፈሱን እንደጠበቀ በዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂና በአቅም ግንባታ በኩል ወደተሻለ ከፍተኛ ደረጃ መድረስ ችሏል።
በኢትዮጵያ ይህንን ጠንካራ የሕዝብ ድጋፍ ያለው እንዲሁም በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም የደራጀ ሠራዊት መኖሩ፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስከበር ብሎም ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ነው።
119ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን “የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል የፊታችን ጥቅምት 15 ቀን 2019 ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት ይከበራል፡፡
በዮናስ ጌትነት