በነፋስ መውጫ ከተማ ለመከላከያ ሠራዊት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ነፋስ መውጫ ከተማ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በሰልፉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር አንድነትንና ሉዓላዊነትን ለማጽናት እያደረገ ያለውን ተጋድሎ የሚደግፍ መልዕክት እያስተላለፉ ነው።
በዚህም በማይነጥፈው የመከላከያ ሠራዊታችን የጀግንነት ተጋድሎ የሀገራችን ክብር ከፍ እናደርጋለን፤ የኢትዮጵያ ጠላቶችን እየደመሰስን ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ እናደርጋለን፤ መከላከያ ሠራዊታችን፣ የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ለከፈሉት ዋጋ ክብር እንሰጣለን የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።
በተጨማሪም መንግሥት ለሰላም መስፈን የሚወስዳቸውን እርምጃወች እንደግፋለን፤ ሀገርን ለማፅናትና ለማበልፀግ ከመንግሥት ጎን እንሰለፋለን፤ መከላከያ ሠራዊታችን የኅብረ ብሔራዊነታችን ማሳያ ዓርማችን ነው ሲሉ ለሀገር ሰላም እና ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ድጋፍ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል