Fana: At a Speed of Life!

ጣና ፎረም: ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ደህንነት ጥናት ተቋም አነሳሽነት፣ የአፍሪካን ሰላምና ጸጥታ ተግዳሮቶች በአፍሪካዊ መፍትሔዎች የመቅረፍ ዋና ዓላማን ይዞ የተመሰረተው ጣና ፎረም በየዓመቱ በባሕር ዳር ይካሄዳል።

የሀገራት መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ የጸጥታ ባለሙያዎች እና ዓለም አቀፍ አጋሮችን ጨምሮ ከመላው ዓለም የሚመጡ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት ፎረሙ ለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካውያንን ማዕከል ያደረጉ መፍትሔዎችን ለመቅረጽ ያለመ ነው፡፡

በሰላም ግንባታ፣ በደህንነት እና ጸጥታ፣ በዘላቂ ልማት እና በተግባራዊ ግጭት አፈታት ዘዴዎች ላይ ውይይቶች ይደረጋሉ።

የጣና ፎረም ዋና ዓላማ የአፍሪካ መሪዎች፣ ተመራማሪዎች እና የሲቪል ማህበረሰብ አባላት በአህጉሩ ጉዳይ በጥልቀት የሚወያዩበት መድረክ በመፍጠር ተግዳሮቶች እንዲፈቱ የሚያስችል መፍትሄ መፍጠሪያ መድረክ ነው።

የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማዕከል በማድረግ በአሕጉሪቱ ሰላምና ደህንነት ላይ የሚመክረው የጣና ፎረም በስኬት ሲካሄድ ቆይቷል።

12ኛው የዘንድሮው የጣና ፎረም ”አፍሪካን ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የቀጣናዊ ፖለቲካዊ ሽግግር” በሚል መሪ ሐሳብ በባሕር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

የጣና ፎረም ለየት የሚያደርገው የአፍሪካ ጉዳዮች በአፍሪካውያን አንደበት የሚንጸባረቁበት መድረክ በመሆኑ የሀገር መሪዎች ሀሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹበትና በአህጉራዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ያለ ውጪ ጣልቃ ገብነት ልምድና ተሞክሮዎችን የሚቀያየሩበት የሚማማሩበት እንዲሁም በጋራ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ የጋራ ውሳኔ የሚሰጡበት ዓመታዊ መድረክ ነው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ማህበረሰቡ ግጭቶችና አለመግባባቶችን የሚፈታባቸው የዛፍ ሥር ውይይቶች መነሻነት በአፍሪካ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ አመላካች የሆኑ ሀሳቦችን የሚዋጡበት የጣና ፎረም የመድረክ አወቃቀርም ከአፍሪካውያን የዛፍ ሥር ውይይት ሀገር በቀል ልምድ የተቀዳ ነው፡፡

“ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” የሚል ማጠንጠኛ ያለው ጣና ፎረም ለአፍሪካውያን ዘላቂ ሰላም የሚበጁ አፍሪካዊ ሀሳቦች የሚፈልቁበት በአህጉሩ በመደበኛ የሰላምና ጸጥታ ሰነዶች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።

አካታች የሆነው ይህ ፎረም በእውነታዎች ላይ በመመስረት የሚከሰቱ ዓለም አቀፍ ለውጦችን መቆጣጠር እና መቋቋም የሚያስችል አህጉራዊ ቁመና መፍጠር ክፍተት ማጥበብ መዋቅራዊ ተጋላጭነቶችን መመርመር፣ ቀጣናዊ ማዕቀፎችን ማጠናከር የሚያስችል ነው።

ሂደቱ በትምህርት ተቋማት እና በሰላም ግንባታ ባለሙያዎች በተዘጋጁ ጥልቅ ጥናት እና ምርምሮች፣ እንዲሁም ውይይቶች የተደገፈ ነው።

ጣና ፎረም ከተለመደ ዓመታዊ የውይይት መድረክ ባለፈ የአፍሪካን የጸጥታ ትርክት እና የፖሊሲ አቅጣጫ በመቅረጽ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡

ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላትን ከአህጉራዊ መሪዎች ጋር በማስተናገድ ፎረሙ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ገንቢ ትብብር እንዲኖር አድርጓል፤ ይህም ውጫዊ ድጋፍ የአፍሪካን ነፃነት ማክበሩንና ማጠናከሩን ያረጋግጣል።

ለዚህም ፎረሙ አህጉራዊ አመለካከቶችን ወደ ዓለም አቀፍ መድረኮች ለማድረስ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ከአፍሪካዊያን ጋር የሚጣጣሙ ርዕዮችን መለየት የሚያስችላቸው አውድ ፈጥሯል።

ባለፉት ፎረሞች የተደረጉ ውይይቶች አህጉራዊ ስትራቴጂዎች የጸጥታ የኢኮኖሚ እና የሉዓላዊነት ተግዳሮቶችን እንዲቋቋሙ ለማድረግ ረድተዋል።

የዘንድሮው ጣና ፎረምም በአፍሪካ ዙሪያ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልጽግናን ለማስፈን የሚረዳ ዕውቀትን ከፖሊሲ ጋር ለማቀናጀት እጅግ አስፈላጊ መድረክ ሆኖ ቀጥሏል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በምሕረት ደምሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.