ድል አብሣሪው ሠራዊት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብሎሽ ለእኛ ዘመን የደረሰችውና ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን የተረከባት ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ በየትውልዱ ብዙ ፈተናዎች ገጥመዋታል።
በእኛ ዘመንም የውጭ ጠላቶች እና የውስጥ ባንዳዎች “ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን” የሚል ዓላማና መፈክር በጋራ በመቅረጽ ‘ኢትዮጵያን ለማፍረስ’ ያስችለናል ያሉትን የሎጀስቲክስ፣ የፋይናንስና የጦር መሣሪያ ድጋፍ በማሰባስብ ተባብረው በከበባ ሥር ሊያውሉንም አሲረዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ 119ኛውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን ምክንያት በማድረግ ለ”መከታ” መጽሔት በሰጡት መግለጫ ባስተላለፉት መልእክት÷ ጠላቶቻችን በተሳሳተ ስሌት ሀገራችን ላይ የከፈቱትን ጥቃት በአጭር ጊዜ አምክነን፤ የምትፈርሰው ኢትዮጵያ ሳትሆን ጠላቶቿ መሆናቸውን፣ የሚሸነፈው ጀግናው መከላከያ ሠራዊቷ ሳይሆን እነሱ ኢትዮጵያ ላይ የእብሪት ጦርነት የከፈቱት ሴረኞችና የጥፋት ኃይሎች መሆናቸውን በተግባር አሳይተናል ብለዋል።
የተፈጥሮ ሃብታችንን ለመጠቀምና ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር በቁርጠኝነትና በሙሉ አቅማችን በተንቀሳቀስንበት በአሁኑ ወቅት፤ ታሪካዊ የውጭ ጠላቶች ከውስጥ ከሀዲዎች ጋር በመቀናጀት ሀገራችንን ከዕድገት ጉዞዋ ለማደናቀፍ እና ለማፍረስ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት፥ የሩቅና የቅርብ ጠላቶቻችን ዘመኑ ያፈራቸውን ቀላልና ከባድ፤ የአየርና የምድር አውዳሚ የጦር መሣሪያዎችንና ተተኳሾችን ኢትዮጵያን ያፈርሱልናል ላሏቸው ወንበዴዎች እና አሸባሪ ቡድኖች በገፍ አስታጥቀዋል።
“ኢትዮጵያ በቀናት ግፋ ቢል በወራት ውስጥ ትበታተናለች” ሲሉ ፍላጎታቸውን እና እቅዳቸውን በይፋ ማወጃቸውን አውስተዋል።
እነዚህ ጠላቶቻችን የጠመቁልንን የጥፋት ሴራና የደቀኑብንን አደጋዎች ለመመከትና ሀገራችንን ከውድቀት፣ ሕዝባችንን ከውርደትና ከመከራ ለመታደግ በጽናት የቆመውን ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንን “እናፈርሰዋለን” የሚል ቅዠት እንደነበራቸውም አስታውሰው፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እኛ የጠላቶቻችንን ዛቻና ድንፋታ እየመረመርን፣ ሴራቸውን የሚያመክን የዝግጁነት ሥራ ስንሠራ ቆየን እንጂ እንደነሱ አልፎከርንም፤ በየአውደ ውጊያው በጠላት ላይ የደረሱትን ኪሳራዎችና የወገንን ተአምራዊ ድሎች በማስተጋባት እንደ ጠላቶቻችን ከበሮ አልደለቅንም ሲሉም የሠራዊቱን ባሕርይ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጠላትን እንቅስቃሴ እንደ ንስር ዓይን ንቁ በሆነ ክትትል፣ ጦርነትን በሩቅ በማስቀረት እና ጦርነት ከተከፈተም በአጭር ጊዜ ውስጥ አጥፊዎችን በማክሸፍ የላቀ ብቃት ማሳየቱን ነው የተናገሩት።
ሠራዊቱ ለሰላም የቅድሚያ ቅድሚያ የሰጠና የሚሰጥ ሲሆን፣ የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ሲደፈር ግን ጠላትን እንደ መብረቅ በመምታት አሸናፊነቱን በተግባር ማረጋገጡን አብሥረዋል።
ይህ ተአምራዊ ስኬትና ፈጣን የድል አብሳሪነት በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተከናወኑት የመከላከያና የፀጥታ ኃይላችን ዘመናዊ የሪፎርም ሥራዎች ውጤት ነው።
የሀገራችን መከላከያ ሠራዊት በመሬት፣ በአየር፣ በባህር፣ በሳይበር እና በስፔስ የውጊያ መስኮች የላቀ ዝግጁነት ያለው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ጥበብ የተደራጀ እና የተቀናጀ ዕዝ በመገንባቱ የጠላትን እንቅስቃሴ ከሩቅ የማወቅና ቅጽበታዊ ምላሽ የመስጠት አቅሙ በእጥፍ አድጓል።
ዘመናዊ ድሮኖችን፣ የሳይበር ደህንነት ስልቶችንና አውቶሜትድ የክትትል ቴክኖሎጂዎችን ከሠራዊቱ የውጊያ ዲሲፕሊንና ጀግንነት ጋር በማጣመሩ፣ ማንኛውንም የጥፋት ስሌት በአጭር ጊዜ ውስጥ የማክሸፍና ድል አብሳሪነቱን አጠናክሮ የመቀጠል ብቃቱ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ደርሷል።
119ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በትላንትናው ዕለት መከበሩም ከፍተኛ ታሪካዊ ፋይዳ አለው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን የሀገራችንን ሰላም፣ ሉዓላዊነት እና የሕዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲሉ በምድር፣ በአየርና በባህር የተሰለፉ አርበኞቻችን የታወሰበት እና የተመሰገነበት፣ ሠራዊታችን የትውልድ ቅብብሎሽ፣ የዲሲፕሊን ጥንካሬ እና የሕዝብ ወገንተኝነት የተደነቀበት ታላቅ ዕለት ነው።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባስተላለፉት መልዕክት እንደጠቆሙት÷ ድል አብሳሪው የኢትዮጵያ መከላከያና የፀጥታ ኃይል እስካለ ድረስ ኢትዮጵያን የሚያፈርስ፣ የዕድገት ጉዞዋን የሚያደናቅፍ፤ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት የሚያደርገውን ጉዞ የሚገታ ኃይል ሊኖር አይችልም።
በአሰፋ አሕመድ