የመቐለ ከተማን የትራፊክ እንቅስቃሴ ሕግ ለማስከበር እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመቐለ ከተማን የትራፊክ እንቅስቃሴ ሕግ ለማስከበር እየተሰራ ነው አሉ የከተማዋ የትራፊክ ፖሊስ አባላት።
ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በፈጠረው ሕገ-ወጥ ተግባር ይስተዋል የነበረውን የትራንስፖርት ፍሰት ክፍተት ለማስተካከል ሕግ የማስከበር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የከተማዋ የትራፊክ ፖሊስ አባላት ገልጸዋል።
የከተማዋ የትራፊክ ፖሊስ አባል ምክትል ኮማንደር ጠዓመ በርሀ እንዳሉት፥ ሰላም በማጣት ምክንያት የመቐለ ከተማ ጎዳናዎች የትራፊክ ሁኔታ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጋልጠው ቆይተዋል ብለዋል።
በተለይም ሰሌዳ የሌላቸው ተሽከርካሪዎችና መንጃ ፈቃድ የሌላቸው አሽከርካሪዎች የበዙበት የዘፈቀደ የትራፊክ ፍሰት አጋጥሞ እንደነበር አንስተው ከሕግና ስርዓት ውጭ ሆኖ የቆየውን የትራንስፖርትና የትራፊክ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ ሕግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን በተፈጠረው ጸጥታና መረጋጋት የትራፊክ ፖሊስ ወደ ሥራ ሲገባ ህብረተሰቡ የነበረውን የአደጋ ስጋት አስወግዶ፣ ተስፋ ሰንቆ የንግድና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን መጀመሩን ምክትል ኮማንደር ጠዓመ አስረድተዋል።
ሕገ-ወጥ ሥራዎች በመበራከታቸው ምክንያት በትራንስፖርት ዘርፉ አደጋ ሲደርስና ወንጀሎች ሲፈጸሙ ቆይተዋ ያሉት ሌላኛው የከተማው የትራፊክ ፖሊስ አባል ሳጅን አብርሃም ካሱ በበኩላቸው በዚህም ማህበረሰቡ ለተለያዩ ችግሮችና እንግልት መዳረጉን አስታውሰው አሁን ሕግን የማስከበር ስራ መጀመሩ ለህዝቡ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ አባላቱ ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ሳጅን አብርሃም፤ ህብረተሰቡ ከሕገ-ወጥ አሰራር ራሱን እንዲጠብቅና ሕግ የማስከበሩ ተግባር ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል።
አሽከርካሪዎች ሕግና ሥርዓት እንዲጠብቁ ለማድረግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ ሳጅን መዓርግ አሰፋ ናቸው።
የከተማው የትራፊክ ፖሊስ አባላት፤ በሕግ መሰረት ፍሰቱ ወደ ነበረበት ለመመለስ እና ከአደጋ ነጻ የሆነ የትራንስፖርት ፍሰት እንዲኖር የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለንም ብለዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡