የትግራይ ተስፋ – ከግጭት ወደ ሰላም፤ ከስቃይ ወደ ልማት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይን ህዝብ ለዓመታት ሲጨቁንና ሲረግጥ የቆየውን ህገወጡ የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሰራዊታችንና በሰላም ኃይሎች አከርካሬውን ተመትቶ ከተበተነ በኋላ፣ ሕዝቡ ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት የተሸጋገረበት አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል።
የፌዴራል መንግሥት የክልሉ ህዝብ ከነበረበት ጭቆና እና አፈና እንዲወጣ እንዲሁም በግጭት ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ የህዝብ አገልግሎቶችን መልሶ የማስጀመር፣ ሰብዓዊ እርዳታ እና መድኃኒት በአስቸኳይ እንዲገባ እና የአካባቢውን አስተዳደር የማቋቋም ፈጣን ርምጃዎች ለህዝቡ እፎይታ ሰጥተዋል።
የፌዴራል መንግሥት በወሰዳቸው ፈጣንና ቆራጥ የሕግና የአደረጃጀት ርምጃዎች የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በፍጥነት ማነቃቃት ተችሏል።
በግጭቱ ወቅት ተቋርጠው የነበሩት የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክ፣ የኤሌክትሪክ፣ የጤና እና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ደረጃ በደረጃ ሙሉ በሙሉ በመመለሳቸው፣ የዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ወደ ነበረበት መደበኛ መስመር ተመልሷል።
ወጣቶች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ ተደርገው በግዳጅ እንዲዘምቱ እና የትምህርት ተቋማትም ለወታደራዊ አገልግሎት ሲውሉ ቆይተዋል፡፡ ይህ ጉዳይ አሁን በፍጥነት እየተፈታ ሲሆን መንግሥት በልዩ ትኩረት ትምህርትን መልሶ የማስጀመር ጥረቶች እያደረገ ነው፡፡
የወደሙ የትምህርት ተቋማትን የመጠገን እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችና መምህራን ወደ ገበታቸው የመመለሱ ስራ በስፋት እየተካሄደ ነው። ለአብነትም በመቐለ ከተማ የመማር ማስተማር ሥራ ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም በድጋሚ ተጀምሯል፡፡
በተመሳሳይ የመቐለ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም መማር ማስተማር በመጀመራቸው ለወጣቱ አዲስ የተስፋ ብርሃን ፈንጥቋል።
የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የባለአደራ አስተዳደር በፍጥነት በማቋቋም ሰላምና መረጋጋት የመፍጠርና መንግሥታዊ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ለማድረግ ችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየአካባቢው አስተዳዳሪዎች በህዝብ እንዲመረጡ የማድግ ተግባራት ተካሂደዋል፡፡
የመሠረተ ልማት ዝርጋታና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች መጀመር ለክልሉ አዲስ የኢኮኖሚ እና የልማት ተስፋ ፈንጥቋል።
በሰላም እጦት እና በጭቆና ሲሰቃይ የቆው የትግራይ ህዝብ ህገወጡ ቡድን ከጫንቃው ላይ ሲወገድለት ለመከላከያ ሠራዊታችን ያለውን ድጋፍ በአደባባይ የገለጸ ሲሆን፤ የትግራይ ህዝብ ፍላጎት ሰላም እና ልማት እንደሆነም አሳይቷል።
ይህ የህዝብ ጥያቄ ከመንግሥት በኩል ፈጣንና ቁርጠኛ ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡
በአጠቃላይ፣ ሕዝቡ ከጦርነት አሰቃቂ ጠባሳዎች በመላቀቅ ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
የተጀመረው ሰላምና የመልሶ ግንባታ ጉዞ፣ የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን የበለፀገችና ሰላማዊት ሀገር የመገንባት ሚናውን የሚወጣበት እድል አግኝቷል።
በቴዎድሮስ ሳህለ