ለ5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የማህብረሰብ ጤና ጉባኤ በቂ ዝግጅት ተደርጓል -ዶ/ር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ለሚካሄደው 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የማህበረሰብ ጤና ጉባኤ በቂ ዝግጅት ተደርጓል አሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፡፡
ዶ/ር መቅደስ ዳባ ዝግጅቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ጉባኤው የጤና ሥርዓታችንን ለሌሎች ለማሳየት እና ከሌሎች ሃገራት ልምድ ለመውሰድ ያግዛል ብለዋል፡፡
ጉባኤው ቀጣናዊ የጤና ትብብርን እንደሚያጠናክር ገልጸው፤ የሃገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ፣ የጤና ዲጂታይዜሽን እና የጤና ቱሪዝምን ለማስፋፋት የአፍሪካ ሃገራት የሚመክሩበት ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጂያን ካሲያ በበኩላቸው፤ ጉባዔው የአፍሪካ የጤና ዘርፍ የደረሰበትን ደረጃ የምናሳይበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
ጉባኤው ከህዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙበት ይጠበቃል፡፡
በዙፋን ካሳሁን