ሱ-35 ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች የኢትዮጵያን ወታደራዊ አቅምና ቀጣናዊ ሚና የሚያሳድጉ ናቸው-እስራኤላዊው ጋዜጠኛ ኤዲ ኮሄን
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሩሲያ የተቀበለቻቸው ሱ-35 (Su-35) ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች ወታደራዊ አቅም እና በቀጣናው ያላትን ሚና በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድጉ ናቸው አሉ የእስራኤሉ ቻናል 14 ጋዜጠኛ እና ተመራማሪ ኤዲ ኮሄን።
ኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን 12 የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች ባለፈው ሳምንት ከሩሲያ ተረክባለች።
የእስራኤሉ ቻናል 14 ጋዜጠኛ እና ተመራማሪ ኤዲ ኮሄን ይህን አስመልክቶ ፥ ኢትዮጵያ የነበሩባትን መሰናክሎች በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶቿ እና በጠንካራ ዓለም አቀፍ ግንኙነቷ በመሻገር ከሩሲያ ጋር የነበራትን ስምምነት በተሳካ ሁኔታ መፈጸም መቻሏን ተናግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ግንኙነቷን የመምራት እና ስትራቴጂካዊ ጥቅሟን የማስከበር አቅሟ ማደጉን በግልጽ የሚያሳይ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሩሲያ የተቀበለቻቸው ሱ-35 ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች ወታደራዊ አቅም እና በቀጣናው ያላትን ተፅዕኖ በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድጉ ናቸው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የግብፅና የዐረብ መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ወታደራዊ ዕድገት በቅርበት እየተከታተሉት እንደሚገኙና አገሪቱ አየር ኃይሏን ማጠናከሯ በግብፅ በኩል ትልቅ ስጋት መፍጠሩን አንስተው ፤ የግብፅን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተችተዋል።
ግብጽ ቀጣናዊ ለውጦችን የሚመጥን ግልጽ የፖለቲካ ርዕይ እንደሚጎድላትና እየጨመረ የመጣው የውስጥ ኢኮኖሚ ውጥረት እና የፖለቲካ ፈተናዎች የግብፅ አመራር ሃገሪቱን የመምራት ብቃት ላይ ጥያቄዎችን እያስነሳ እንደሚገኝ አመልክተዋል።