በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዛሬ 9 ጨዋታዎች ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የ4ኛ ዙር መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ዘጠኝ ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
በዚህም ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ሪያል ማድሪድ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ከኤኢኬ አቴንስን ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
በአሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆ የሚመራው ሪያል ማድሪድ በዚህ ውድድር ዓመት በሻምፒየንስ ሊጉ ያደረጋቸውን ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች በሙሉ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
ተጋጣሚው ኤኢኬ አቴንስ በበኩሉ በሻምፒየንስ ሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፎ በአንዱ ብቻ ድል አድርጓል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድር እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አራት ጨዋታዎች በተመሳሳይ አንድ አንድ ጊዜ ድል ሲያደርጉ በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በተመሳሳይ ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ሊቨርፑል ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ከፌነርባቼ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
ሊቨርፑል በዚህ የውድድር ዓመት በሻምፒየንስ ሊጉ ያደረጋቸውን ሦስቱን ጨዋታዎች አሸንፏል፡፡
ባለሜዳው ቡድን ፌነርባቼ በበኩሉ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ የሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታውን ለማሸነፍ የሚያደርገው ፉክክር ይጠበቃል፡፡
ምሽት 5 ሰዓት ላይ ማንቼስተር ሲቲ ወደ ጀርመን አቅንቶ በሬድ ቡል አሬና ስታዲየም ከአርቢ ሊፕዚሽ ጋር ይገናኛል፡፡
ማንቼስተር ሲቲ በውድድር ዓመቱ በሻምፒየንስ ሊጉ ተከታታይ ድሉን ለማሳካት ይፋለማል፡፡
አርቢ ሌፕዚሽ በበኩሉ በሪያል ማድሪድ ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርገው ፉክክር ተጠባቂ ነው፡፡
በተመሳሳይ ምሽት 5 ሰዓት ላይ የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ከስላቪያ ፕራህ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
አርሰናል ከባየርን ሙኒክ ጋር 2 አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በኋላ በሻምፒየንስ ሊጉ ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል፡፡
ቦርሲያ ዶርትሙንድ ከሪያል ቤቲስ፣ ፒኤስቪ ከክለብ ብሩዥ፣ ፖርቶ ከናፖሊ፣ ሌንስ ከኮሞ እንዲሁም ቫይኪንግ ከሳባህ ሌሎች ምሽት 5 ሰዓት ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡