Fana: At a Speed of Life!

የመደመር መንግሥት በትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ውጤት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት በትምህርት ጥራት፣ ተሳትፎና የተማሪዎች ውጤት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው አሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ።
አቶ ኦርዲን በድሪ በክልሉ ከተማና ገጠር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የ2019 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምገባ መርሀ-ግብርን በይፋ አስጀምረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት፤ የመደመር መንግሥት በትምህርት ጥራት፣ በተሳትፎና በተማሪዎች ውጤት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚነኝ በማንሳት ባለፉት ዓመታትም በዘርፉ የተከናወኑት ተግባራት እጅግ አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በተለይም በትምህርት ቤቶች የሚከናወነው የተማሪዎች ምገባ የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ በማሳደግ፤ የትምህርት መጠነ-ማቋረጥን በማስቀረት እና የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል አቅም እንዲጨምር በማድረግ በአጠቃላይ ውጤታማነት እንደሚያሻሽል ጠቁመዋል፡፡
ለትምህርት ዘመኑ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም የክልሉ መንግስት ከ46 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መመደቡንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
ለመርሐ ግብሩ ዘላቂነት ባለሃብቶች፣ አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት እየሰጡት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም መርሐ ግብሩ በማህበራት ለተደራጁ እናቶች የሥራ እድል በመፍጠር የቤተሰብ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ አስችሏል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በክልሉ ከተማና ገጠር በሚገኙ 68 ትምህርት ቤቶች ከቅድመ-መደበኛ እስከ 4ኛ ክፍል የሚማሩ 40 ሺህ 672 ተማሪዎች የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.