በአማራ ክልል ሰብል የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 29፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ቀድመው የደረሱ ሰብሎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል አሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)።
ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) ፥ በክልሉ የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበትና የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ ከላይ እስከ ታች ባለው አመራርና ሙያተኛ በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በቴክኖሎጂ በታገዘ አግባብ ፈጣንና ውጤታማ በሆነ መንገድ ሰብል የመሰብሰብ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በግብርና ኤክስቴንሽን አርሶ አደሩን አስቀድሞ የማዘጋጀት ሥራ መጠናቀቁንና ሰብሎችን ለመሰብሰብ ከ80 በላይ ኮምባይነሮች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በክልሉ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎንደር እንዲሁም ሰሜን ሸዋ አካባቢዎች የስንዴ ምርትን በኮምባይነር የመሰብሰብ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቀጣይም ተጨማሪ ኮምባይነሮችን ለማስገባትና ክልሉ የያዘውን የአምስት ዓመት ግብ ለማሳካት እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ንጉሴ ማለደ በበኩላቸው፤ በዞኑ በመኽር ወቅቱ በሰብል ከለማው 586 ሺህ ሄክታር 187 ሺህ ሄክታሩን መሰብሰብ መቻሉንና ከ24 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል።
አብዛኛው የማሳ ሰብል በመድረስ ላይ ያለ በመሆኑ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በንቅናቄ ሰብል የመሰብሰብ ሥራዎች በስፋት የሚከናወን መሆኑንም አስረድተዋል።