Fana: At a Speed of Life!

የቻይና እና የሩሲያ መሪዎች ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ እና የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቻይና ሼንዤን ተገናኝተው ተወያይተዋል።

የሁለቱ ሀገራት ፕሬዚዳንቶች ተገናኝተው የተወያዩት ከእስያ-ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ ጎን ለጎን ነው።

ይህ ውይይት የተካሄደው ሁለቱ መሪዎች ሐሙስ ዕለት ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የሦስትዮሽ ጉባኤ ከሚያካሂዱበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሲሆን፤ የውይይታቸው ዝርዝር ጉዳይ ይፋ አልሆነም።

የቻይና እና የሩሲያ የዜና ወኪሎች እንደዘገቡት፤ የአሁኑን ውይይት ጨምሮ ሁለቱ መሪዎች በፈረንጆቹ 2026 ብቻ ለአምስተኛ ጊዜ ተገናኝተዋል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ከፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ እና ከትራምፕ ጋር የምናደርገው የሦስትዮሽ ውይይት እጅግ ጠቃሚ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡

ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስጋቶች እየጨመሩ ባሉበት በዚህ ወቅት በእጅጉ የሚያስፈልገው ከመከፋፈል ይልቅ አንድነት እንዲሁም ከማስጠንቀቂያ ይልቅ ውይይት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በበኩላቸው፤ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በነፃ ንግድ ዙሪያ ሰፊ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ቻይና ታሪፍ በመቀነስ፣ የገበያ ተደራሽነትን በማስፋት እንዲሁም ደንቦችንና የአስተዳደር መመዘኛዎችን በመፈተሽ ጥልቅ ማሻሻያ ታደርጋለች ሲሉ ቃል መግባታቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

በእመቤት ሲሳይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.