Fana: At a Speed of Life!

የመደመር መንግሥት የከተሜነት ዕሳቤ፣ ከተሞችን የሥራ ዕድል ምርታማነት ማዕከላት እንዲሆኑ ያደርጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት የከተሜነት ዕሳቤ፣ ከተሞችን የሥራ ዕድል ምርታማነት ማዕከላት እንዲሆኑ ያደርጋል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የከተማ ልማት ጥራት የአንድን ሀገር ምርታማነት፣ የሰው ልጅ ክብር፣ ማኅበራዊ ሥርዓት እና የአካባቢን ችግር የመቋቋም ዐቅም መገለጫ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።

በመሆኑም የመደመር መንግሥት የከተሜነት ዕሳቤ፣ ከተሞችን የሥራ ፈጠራ፣ የንግድ፣ የዕውቀት፣ የባህል፣ የተቋማት እና የሥራ ዕድል ምርታማነት ማዕከላት እንዲሆኑ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህም ለወደፊት የሕዝብ ቁጥር ዕድገት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ክስተቶች፣ ለመሠረተ ልማት ፍላጎቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ ምላሽ ለመስጠት ታስቦ በዕቅድ የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል።

ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ይፋ በተደረጉት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ላይ በመመሥረት፣ ዛሬ 57 ሄክታር የሚሸፍነውን የኮሪደር ልማት በይፋ አስጀምረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከቦሌ መድኃኔዓለም በጎላጉል እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ፣ ከቦሌ መድኃኔዓለም እስከ ሞኤንኮ፣ ከቦሌ ትምህርት ቤት እስከ አደይ አበባ ሞዴል መንደር፣ ከኢምፔሪያል ሆቴል እስከ ሻላ ፓርክ፣ ከቺቺኒያ እስከ ቦሌ ሩዋንዳ፣ ከአደይ አበባ ስታዲየም እስከ ቦሌ መንገድ እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ማካተቱን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ለአረንጓዴ እና ዘመናዊ የከተማ ልማት አዲስ መሥፈርት እንደሚያስቀምጥ ገልጸው፤ ዘመናዊ መንገዶችን፣ ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶችን፣ የብስክሌት መሥመሮችን፣ የመሬት ውስጥ መሠረተ ልማቶችን፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን እንደያዘ አመልክተዋል።

ከ5 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችሉ የመኪና ማቆሚያዎችን እንደሚያካትት ጠቅሰው፤ በተጨማሪም የታደሱ ትምህርት ቤቶችን፣ ቤተ መጻሕፍትን፣ የመጨዋቻ ሥፍራዎችን፣ የስፖርት ሜዳዎችን፣ ካፌዎችን፣ ሬስቶራንቶችን እና ፕላዛዎችን የያዘ ሲሆን፣ ሰዎችን፣ ሰብአዊ ክብርን እና የኑሮ ጥራትን የከተማ ልማት ዋነኛ ማዕከል አድርጓል ብለዋል።

ይህ ከመሠረተ ልማት ግንባታ በላይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ለአዲስ አበባ እና ለኢትዮጵያ ከተሞች መጻኢ ዕድል የተነደፈ ሰፊ ራዕይ አካል ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ይኸውም ምርታማትን፣ አካታችነት፣ አረንጓዴነትንና የማይበገር ልማትን ያካተተ ነው፤ ክንውኑም በሕዝቦቻችን ፍላጎት እና በመጪው ትውልድ መሻት ዙሪያ የተቃኘ ነው ብለዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.