የመዲናዋን ዕድገትና ዘመናዊነት የሚመጥን ደንብ ማስከበር አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባን ዕድገትና ዘመናዊነት የሚመጥን የደንብ ማስከበር አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም ተገንብቷል አለ የከተማዋ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ፡፡
ባለስልጣኑ ለ7 ሺህ 905 የደንብ አስከባሪ ኦፊሰሮችና ለ159 አመራሮች በአሥር ተከታታይ ዙሮች የሚሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና አስጀምሯል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮና ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶችን ተግባራዊ አድርጓል፡፡
በተለይም በዕውቀትና በብቃት የበለጸጉ ኦፊሰሮችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።
ስልጠናው የከተማዋን ዕድገትና ዘመናዊነት የሚመጥን የደንብ ማስከበር አገልግሎት ለመስጠት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያከበረ አገልግሎት መስጠት፣ የጋራ ተግባቦትና ተሳትፎን ማጠናከር፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን መታገል እንዲሁም ቴክኖሎጂያዊ አሠራርን ማስረጽ የስልጠናው ዋና አላማዎች ናቸው።
ሠልጣኞች በሥልጠናው የሚያገኙትን የንድፈ ሐሳብና የተግባር ዕውቀት ወደ መሬት በማውረድ ለተቋሙ ውጤታማነት ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡