ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሚገኙበት መደበኛ ጉባኤውን በመጪው ሐሙስ ያካሂዳል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚገኙበት በመጪው ሐሙስ ያካሂዳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ እንደሚሰጡ ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ምክር ቤቱ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በሚያካሂደው መደበኛ ጉባኤው ላይ የመንግሥትን አቋም ካዳመጠ በኋላ የድጋፍ ሞሽን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡
በዕለቱ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች እንግዶች በክብር እንግድነት ይታደማሉ።