ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል መሆኗ የአቪዬሽን ደህንነት ተልዕኮን ለማሳካት ያግዛል – አገልግሎቱ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ም/ቤት አባል ሆና መመረጧ የአቪዬሽን ደህንነት ተልዕኮን ለማሳካት እገዛ ያደርጋል አለ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፡፡
ኢትዮጵያ በሞንትሪያል ካናዳ በተካሄደው የድርጅቱ 43ኛ ልዩ ጉባኤ ላይ የምክር ቤቱ አባል ሀገር ሆና መመረጧ ይታወሳል፡፡
አገልግሎቱ ባስተላለፈው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት፤ መንግሥት ለአቪዬሽን ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረትና እንደ ሀገር በተደረገው ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የተገኘ ድል መሆኑን አመልክቷል፡፡
የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻልን ጨምሮ በተከናወኑ ሁለንተናዊ ሪፎርሞች በተከታታይ ዓመታት በአቪዬሽን ደህንነት በተመዘገቡ ተጨባጭ ስኬቶችና ለዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተገዢ የመሆን ዕይታን ማጎልበት መቻሉ ኢትዮጵያን ተመራጭ እንዳደረጋት አመልክቷል፡:
ሀገራችን በዘርፉ የደረሰችበትን ዕድገትና ከኢትዮጵያ አየርመንገድ ተወዳዳሪነት ጋር የሚመጣጠን ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ተከትሎ የተገኘው የምክር ቤት አባልነት የአቪዬሽን ደኅንነትን የማረጋገጥ ተልዕኮውን ለማሳካት እንደሚያግዘውም አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በአባልነት ከነበራት ተሳትፎ በተጨማሪ በድርጅቱ የውሳኔ ሰጪነት ሚናዋን ከፍ በማድረግ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ተቋም ለመሆን የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ነው አገልግሎቱ የገለጸው፡፡