ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን መስከረም 21 ቀን በብሔራዊ ደረጃ ይከበራል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም ዓቀፍ የአረጋውያን ቀን መስከረም 21 ቀን ‘ወቅታዊ እና ተግባራዊ ምላሽ ለአረጋውያን’ በሚል መሪ ቃል በብሔራዊ ደረጃ እንደሚከበር ተገልጿል፡፡
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አረጋውያን ጡረተኞች ብሔራዊ ማህበር በጋራ ዓለም ዓቀፍ የአረጋውያን ቀን በዓለም ለ30ኛ ጊዜ በብሔራዊ ደረጃ ደግሞ ለ29ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡
እለቱ ቃሊቲ በሚገኘው የአረጋውያን እንክብካቤና ልማት ማዕከል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በክብረ በዓሉ የፓናል ውይይት፣ በኮሮና ወረርሽኝን የስነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው አረጋውያንና የጤና ባለሙያዎች ክብርና እውቅና ሚሰጥ ሲሆን በየክልሉና በፌደራል ከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ አረጋውያንና ለአረጋውያን ተቋማዊ አገልግሎት ለሚሰጡ ድርጅቶች የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አረጋውያን በተለያየ ጊዜ ለተለያዩ ማህበራዊ ሳንካወች ሲጋለጡ እንደነበር ገልጸው፤ በአረጋውያን ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገር ላይም ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ሁሉም አረጋውያንን በመንከባከብ የትውልድን ቀጣይነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሌ በበኩላቸው አረጋውያን ላይ የሚደርሱ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ እና አረጋውያን ለተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተጋለጡ በመሆኑ መንግስት፣ ህብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡