አቶ ሽመልስ አብዲሣ የኢሬቻ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 21 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚደንት አቶ ሽመልስ አብዲሣ የ2013 ዓ.ም የኢሬቻ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የታላቁ የኢሬቻ በዓል ባለቤት የሆንከዉ የኦሮሞ ህዝብ ሄይ!
የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች
ከሁሉም አስቀድሜ አስቸጋሪዉን የክረምት ወራት አሳልፋችሁ ተስፋ ወደሚሰነቅበት የዐደይ ወራት እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እወደለሁ፡፡
ታላቁ የኢሬቻ በዓል አስቸጋሪዉ የክረምት ወራት አልፈዉ በመጀመሪያዉ የፀደይ ወር የሚከበር የምስጋና እና የይቅርታ በዓል ነዉ፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ የፈጣሪ እጅ ጥበብ የሆነዉን ድንቃድንቅ ተፈጥሮ የሚያደንቅበት እና የሚያሞግስበት ዕለት ነዉ፡፡
ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንደር፤ ብሎም እስከ ሀገር ተከስተዉ ላለፉት በጎም ሆኑ አስከፊ ክስተቶች የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪዉን የሚያመስግንበት ታላቅ በዓል ነዉ፡፡
ለኢሬቻ በዓል የልብና አዕምሮ ንጽሕና ተቀዳሚ ጉዳዮች ናቸዉ፡፡ ቂም እና በቀል፤ ጥላቻና ኩርፊያ ለኢሬቻ በዓል ተጻራሪ ጉዳዮች ናቸዉ፡፡ እነዚህን ሁሉ በይቅርታ ዘግቶ የሚያልፍ በዓል ነዉ፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ በኢሬቻ በዓል ላይ ነገሮችን ሁሉ በሆደ ሰፊነት ይቅር ለሚለዉ ፈጣሪ የተማፅኖ መልዕክቱን ያደርሳል፡፡ በምድር ላይ እና ከምድር በላይ ያሉ ድንቃ ድንቅ የፈጣሪ እጅ ሥራዎች ሁሉ ይከበራሉ፡፡ የልብ ንፅህና እና ይቅር ባይነት ይዘመራል፡፡ኢሬቻ የሰላምና የእርጋታ በዓል ነዉ፡፡ ኢሬቻ ቂምና ጥላቻን በይቅርታ የሚያክም ታላቅ በዓል ነዉ፡፡ የአንድነትና የተስፋ ተምሳሌት ነዉ፡፡
የፀደይ ወራት በኦሮሞ ዘንድ እንደ ዉበት ተምሳሌት ይቆጠራል፡፡ የፈጣሪ ድንቃድንቅ ሥራዎች የሚደነቅበት ወር ነዉ፡፡ ዉጣዉረድ የበዛበት የክረምት ወር አልፎ፤ የተዘራዉ አዝመራ ለፍሬ በቅቶ፤ የሰዉን ልጅ በተስፋ የሚሞላበት ዉብ የሆነ ወር ነዉ፡፡ የፈጣሪ ድንቅ የሽግግርና የተስፋ ወር የሆነዉን የእሬቻ ክብረ በአል መሬሆ፣ መሬሆ እየተባለ የሚደነቅበት የብርሃን እለት ነዉ፡፡
ዘንድሮ በኮሮና በሽታ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ምክንያት ፈተና ዉስጥ ሆነን የምናከበረዉ የእሬቻ በአል እንደተለመደዉ በብዛት ወጥተን ሚሊዮን እጆችን በመዘርጋት ለማክበር ብንቸገርም፤ በጊዜያዊ ጨለማ ተጋርደን ከፊት ለፊታችን ወዳለዉ ታላቅ ብርሃን እያማተርን እናከብረዋለን፡፡ ይህ የፈተና ምእራፍ አልፎ የፈካ ብርሃን እንደምናይ እና የተደላደለ ህይወት የምንኖርበት ጊዜ እንደሚመጣ አንጠራጠርም፡፡
ኦሮሞ ሊህቆች አሉት፡፡ የሃሳብ ፍጭቶች እንዲኖሩ ይፈቅዳል፡፡ በመደማመጥ ላይ ለተመሰረተ ወይይት ተገዢ ነዉ፡፡ አብሮ መስራትና አብሮ መብላት እንዲሁም ማስተዋልና እዉነትን ማንገስ የጥንት እሴቶቹ ናቸዉ፡፡ የእሬቻ በአል ትዉልድ የሚጎነጨዉ እዉነት የሚፈልቅበት በአል ነዉ፡፡ እዉነተኛ የማንነትና የአንድነት መገለጫ ለሆነዉ የእሬቻ ክብረ በአል ቀን በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ፤ እንኳን አደረሰን ስል በታላቅ ደስታ ነዉ፡፡
የዘንድሮዉን ኢሬቻ በአል ስናከብር በተፈጥሮና በሰዉ ሰራሽ
አደጋዎች ምክንያት ለተጎዱ ወገኖቻችን ያደረግነዉ ድጋፍና ርብርብ በፈጣሪና ፍጥረታት ፊት ጎልቶ የሚታይ የክብርና የሞገስ አርማ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በኢሬቻ ክብረ በአል ወቅት ተፈጥሮ በለገሰችን ድንቅ የአከባቢ ልምላሜ እንደምንረካዉ ሁሉ ካለንና ካፈራነዉ ላይ ለተራቡ፣ ለተጠሙና ለታረዙት እንዲሁም በተፈጥሮና በሰዉ ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ለተቸገሩ ወገኖቻችን መድረስ መቻል መታደል ነዉ፡፡
በበርካታ ፈተናዎች ዉስጥ ሆነን እያከበርን ያለነዉ የዘንድሮ ኢሬቻ በአል ድርብ ትርጓሜ አለዉ፡፡ በገዳ ስርአት እሴቶች መሰረት የኦሮሞ ህዝብ ትዉልድን ሲቀርጽና ብቁ ሲያደርግ በምቾት ዉስጥ ሆኖ በችግር ጊዜ ፈተናን መቋቋም የሚችሉበትን ብቃትና ከችግር የመዉጫ ክህሎቶችን ያስታጥቃል፡፡ የገዳ ስርአት እሴቶችን የወረሰ ትዉልድ በዚህ አመት በተጨባጭ እንዳየነዉ ለፈተና እጁን አይሰጥም፡፡ ያለዉን ተካፍሎ ፤ የበሰለዉን አብሮ ተቋድሶ ተመግቦ ይኖራል፡፡
እኛ አዲሱ ትዉልድ በገዳ ስርዓት ከመኩራራትና ከመመፃደቅ አልፈን ተጨባጭ የሆነ ሥራ እየሰራን ድላችንን ማጣጣም ጀምረናል፡፡ ከፍተኛ ጥረት በጠየቀዉ የትዉልዳችን ጥናትና ምርምር አማካኝነት የገዳ ሥርዓታችን በዓለም የማይዳሰስ የቅርስ መዝገብ (ዩኔስኮ)ላይ እንዲመዘገብ ተደርጓል፡፡ከኦሮሞና ከኢትዮጵያ ሀብትነት ተሸግሮ አለም የሚያደንቀዉ፤የሚንከባከበዉና የሚጠብቀዉ መሆን ችሏል፡፡
የኛ ትዉልድ የገዳ ሥርዓት የትምህርትና ትዉልድ የሚገነባበት እንዲሆን በማድረግ በትዉልድ የሚወረስ ድል አድርጓታል፡፡ ትዉልዱን በትዉስታ ከማዉረስ በጥናት ወደ ማዉረስ ተሸጋግሯል፡፡ በገዳ ሥርዓት እሴቶች በመቀረጽ የሀገርና ሕዝብ ግንባታ ስልጣኔ ለመቀዳጀት ዕድለኛ ሆኗል፡፡
በገዳ ሥርዓት እሴቶች ዉስጥ ሽምግልና ፍትህን ለባለቤቱ መመለስና እዉነትን የመፍረድ ሥርዓት ነዉ፡፡ ስምምነትን የማረጋገጥና የሠላም ምሰሶና የእርጋታ ምንጭም ነዉ፡፡ እኛም የትናንትናዉን ትዉልድ ዉርስ በጥናት አስደግፈን የፍትህ ሥርዓታችን አካል ለማድረግ ተዘጋጅተናል፡፡
ከሁሉም በላይ ከገዳ ሥርዓት እሴቶች የወረስነዉን ሀብት በመጠቀም ሀገርንና ትዉልድን ለመገንባት የጀማመርናቸዉ ሥራዎች እጅግ የሚያኮሩ ናቸዉ፡፡ በኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ዉስጥ ትዉልድ ተልዕኮና ግዳጅ የሚወስድበትና የሚያሰተላልፍበት እሴቶች አሉ፡፡ በገዳ ሥርዓት እሴቶች በመጠቀም የዜግነት አገልግሎት አዋጅ እንደ ሥርዓት የምንመራበት አድርገናል፡፡
ትዉልድን የመገንባት ፤ንጽህናን የመጨመር፤ ቀንና ሌሊት
የመስራት፤ ተወዳዳሪነትን የማሳደግና መተባበርን የማረጋገጥ ዓላማ ያነገበዉ የዜግነት አገልግሎት ሥራዎቻችን ተጨባጭ ዉጤት ማስመዝገብ ጀምሯል፡፡ መተሳሰብን፤ መረዳዳትን ፤አንዱ ለሌላኛዉ መድረስንና መልካም የሥራ ባህልን ማላመድ ጀምረናል፡፡
የሆራ ፊንፊኔ እሬቻ የአያቶቻችንና የቅድመ አያቶቻችን ማስታወሻ ነዉ፡፡ እዉነትን ተናግረን ለእዉነት ቆመን እዉነትን የምንናገርበት ነዉ፡፡ ስለ አዉነት መረጃ የሚወጣበት ነዉ፤ የትዉልድን ክብረ በዓል ስፍራ ማጠናከር ይጠበቅብናል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ለሃገራችንና ለክልላችን ሰላም ዘብ በመቆም ድላችንን ለማደናቀፍ የሚፍጨረጨሩ ሐይሎችን በማጋለጥ ልናሳፍራቸዉ ይገባል፡፡ ለአፍታም ልንዘናጋ አይገባም፡፡ ሰላም በሌለበት ቦታ በእጃችን የገባዉን ድል ማቆየትና ተጨማሪ ድል ማስመዝገብ የሚታሰብ አይሆንም፡፡ ስለሆነም፤ በተባበረ ክንድ ሰላማችንን እናረጋግጥ! በማለት መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
ኦሮሚያን እንገነባለን፣ ኢትዮጵያን ከፍ እናደርጋለን፣ የአፍሪካ ቀንድን እናረጋጋለን!
አመሰግናለሁ! (ሖራ ቡላ ዴባና)
አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት
መስከረም 2013
ፊንፊኔ