ከለውጡ ጋር የተቃኘ የመንግስት ሰራተኛ መገንባት ያስፈልጋል- ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከለውጡ ጋር በአስተሳሰብ ክህሎትና እውቀት የተቃኘ የመንግስት ሰራተኛ መገንባት እንደሚያስፈልግ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።
በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ትምህርትና ስልጠና፣ አሰራርና አደረጃጀት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ ውይይት ተካሄዷል።
በዚህ ወቅት ዶክተር ቢቂላ አሁን በሀገሪቱ የፖለቲካ አስተሳሰብ በመቀየሩ ባለፉት 28 ዓመታት የተጓዝንበትን አገልግሎት አሰጣጥ አካሄድ ይዘን መቀጠል አንችልም ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም ከለውጡ ጋር በአስተሳሰብ ክህሎትና እውቀት የተቃኘ የመንግስት ሰራተኛ መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸው ፤ ለዚህም ወሳኝ የሆኑ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአመለካከት፣ አስተሳሰብና የእውቀት ለውጥ ለማምጣት ደግሞ በክልልና ሀገር ደረጃ ያሉ የአቅም ግንባታ ተቋማት የላቀ ሚና አላቸው ብለዋል።
የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ በሌሎች ክልሎችና ሀገር ደረጃ ያሉ አካዳሚዎች የመንግስት ሰራተኞችን አቅም በመገንባት እንዲሁም የመፈፀምና የማስፈፀም ደረጃ በማሳደግ ረገድ መንግስታዊ መዋቅሮችን ማብቃት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።
የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመቹ አራርሳ በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የሚያስፈልጋቸውን እውቀትና ክህሎት በመለየት ለማብቃት የጥናትና ምርምር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በክልሉ ከተሞች ሪፎርምና ገቢ ማሳደጊያ፣ ሴቶች ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት፣ ሪፎርምና ሀገራዊ ለውጥ ቀጣይነት፣ በተቋማዊ ለውጥና ካይዘን ላይ ከ100 በላይ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ለመንግስት ታትመው መድረሳቸውን አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በማሰልጠኛ ማዕከልነት ከተቋቋመ ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን በአጫጭር ስልጠናና አቅም ግንባታ ከ300ሺህ በላይ የመንግስት ሠራተኞችን ማሰልጠኑን ዶክተር ገመቹ አስታውሰዋል።
ዩኒቨርስቲው በአሁኑ ወቅት በዲፕሎማ፣ መጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ከ11ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ ፕሮግራሞች እያሰለጠነ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።