በኦሮሚያ ክልል 390 የእርሻ ትራክተር እና ኮምባይነር ለአርሶ አደሮች ተሰጠ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 27 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል 390 የእርሻ የትራክተር ለአርሶ አደሮች መሰጠቱ ተገለጸ።
በዚህም በዛሬው እለት በሻሸመኔ 310 የእርሻ ትራክተርና 80 የደረሱ ሰብሎችን የሚያጭድ ኮምባይነር ለአርሶ አደሮች ተሰጥቷል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የብሄራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ፣ የኦሮሚያ የብልጽግና ፓርቲ መሪ አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ትራክተሮቹን እና ኮምባይነሮቹን ለአርሶ አደሮቹ የሰጠው ኬኛ የግብርና መሣሪያዎች ማምረቻና ጠቅላላ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሆኑ ተገልጿል።
ማህበሩ ከዚህ በፊትም በሶስት ዙር 427 ትራክተሮች ለገበሬዎችና ለወጣቶች መስጠቱም ነው የተገለጸው።
ትራክተሮቹ ከ717 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት የሚችል ነው ተብሏል።
ኬኛ የግብርና መሣሪያዎች ማምረቻ ከተቋቋመ ሶስት ዓመት የሞላው ሲሆን የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት ሶስት ዓመታት 737 የእርሻ ትራክተር መኪናና 80 ኮምባይነር ለገበሬዎችና ለወጣቶች መስጠቱንም ነው የተገለጸው።
በዚህ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የሲዳማ ብሄራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ባለፈው በሻሸመኔ ከተማ ለደረሰው የንብረት ውድመት ድጋፍ የሚሆን 3 ሚሊየን 500 ሺህ ብር ሰጥተዋል።
አቶ ደስታ የገንዘብ ድጋፉን ለክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ማስረከባቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።