ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ በአረብኛ ቋንቋ ከሚጽፉ የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ ፣መስከረም 27 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል ዛሬ በአረብኛ ቋንቋ በህዳሴው ግድብ ላይ ከሚጽፉ የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱም ባሉ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች እና በቀጣይ መከናወን በሚገባቸው የትኩረት መስኮች ላይ ምክክር አድርጓል።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ÷ የሚዲያ ባለሙያዎች ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ እያደረጉት ያለውን የሚዲያ እንቅስቃሴ በማድነቅ ባለሙያዎችን አመስግነዋል።
የሚዲያ ባለሙያዎቹ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን አቋም በአረብኛ ቋንቋ ለአረቡ ዓለም የማስተዋወቁ ስራ በስፋት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።
በቀጣይ ተጨማሪ የትኩረት መስኮችን በመለየት መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ከዚህ አንጻር በመካከለኛው ምስራቅና በአረብ ሃገራት በህዝበ ለህዝብ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና መሰል ዘርፎች ላይ በሚዲያና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የሚሰሩ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አስፈላጊ ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።