በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በደረሰ የእሳት አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በተለምዶ ቦሌ ሚካኤል አየር አምባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ትናንት ምሽት ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በአንድ ሰው ላይ ደግሞ ከባድ የቃጠሎ አደጋ ደርሷል፡፡
የእሳት አደጋው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት የከተማው የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የእሳት አደጋ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል፡፡
የአደጋውን መንስዔ እና በንብረት ላይ የደረሰውን ውድመት በተመለከተ ፖሊስና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በማጣራት ላይ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለጠፋው የሰው ህይወት እና ለደረሰው አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል።