የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን በአንበጣ መንጋ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን በአንበጣ መንጋ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ጎብኝተዋል።
ሚኒስትሩ በትናንትናው እለት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን እና በድሬዳዋ አስተዳደር በመገኘት የአንበጣ መንጋው ያደረሰውን ጉዳት መመልከታቸውን በትዊተር ገፃቸው አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካል የሚረጩ 5 ተጨማሪ አውሮፕላኖችን እስከ መጪው ረቡዕ ድረስ ከውጭ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።
ከእነዚህ ውስጥ ሁለት አውሮፕላኖች መግባታቸውን ያስታወቁት ሚኒስትሩ ፥ ሶስተኛው አውሮፕላን ዛሬ ኮምቦልቻ የሚገባ መሆኑንም ገልፀዋል።
የአንበጣ መንጋው በአሁኑ ወቅት በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መከሰቱንም የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።