በሩብ ዓመቱ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ግማሽ ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ግማሽ ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለፀ።
ገቢው የተገኘው ከማምረቻው፣ ከግብርናና ከአገልግሎት ዘርፍ መሆኑም ታውቋል፡፡
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ የኮሚሽኑን የ2013 ዓ.ም ሩብ ዓመት ስራ አፈጻጸም አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በሩብ ዓመቱ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት የታቀደ የነበረ ሲሆን ማሳካት የተቻለው ግን የዕቅዱን ግማሽ ያህል ነው።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ጫናና በተለያዩ የሃገሪቷ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶች ለዕቅዱ አለመሳካት ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ይህም ከዘርፉ መገኘት የነበረበትን ገቢ ከማሳጣቱ ባሻገር ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዳይሆኑም አድርጓል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል በኢንዱስትሪ ፓርኮች የጥሬ እቃ፣ የኢኮኖሚና የምርት መቀዛቀዝ ቢኖርም ወቅቱ የሚፈልገውን ምርት በማምረት ረገድ ስኬታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልፀዋል።
ጥራት ያላቸው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች፣ የእጅ ጓንቶችና የመመርመሪያ ኪቶችን በስፋት የማምረት ስራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።
በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ተቋቁሞ ስኬታማ ስራዎች ለማከናወን በክልልና በከተማ አስተዳደር ከሚገኙ አልሚዎች ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡