መምህራንን የቤት ባለቤት ለማድረግ ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መምህራንን የቤት ባለቤት ለማድረግ ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ መምህራን ለትምህርት ዘርፉ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው ብለዋል፡፡
ይህ ዓለማ ይሳካ ዘንድም መምህራን የተረጋጋ ህይወት መኖር አለባቸው ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፡፡
ለዚህም መንግስት ከዓመታት በፊት የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር መቅረፍ የሚያስችል መርሃ ግብር ይፋ አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ መሰረትም ክልሎች እንደ የአካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ ለመምህራን ቤት ወይም የቤት መስሪያ ቦታ የሚያቀርቡ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ይሁን እንጅ አሁን ላይ የመርሃ ግብሩ አፈጻጸም በሀገር አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን ነው ዶክተር ገረመው የተናገሩት ፡፡
የአፈፃጸሙ ደረጃ ከክልል ክልል፣ ከከተማ ከተማ እንዲሁም ከወረዳ ወረዳ የሚለያይ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዲኤታው ለዚህም በርካታ መንስኤዎች መለየታቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህም የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የመሬት አቅርቦት እጥረት፣ የካሳ ክፍያ ጉዳይ እና ፍትሃዊ ያልሆነ የመሬት እደላ ቀዳሚ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች በፍጥነት በመቅረፍም መምህራንን የቤት ባለቤት ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ