ምክር ቤቱ ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት በሞጣ የተከሰተውን ጉዳይ የሚያጣራ ኮሚቴ ወደ ስፍራው ሊልክ ነው
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 15፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት በሞጣ ከተማ የተከሰተውን የችግር ምክንያትና የጉዳቱን መጠን የሚያጣራ ኮሚቴ ወደ ስፍራው እንደሚልክ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ።
በምስራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ከተማ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ውሉ ባልታወቀ ምክንያት መስጆዶችና የንግድ ተቋማት ላይ የደረሰውን ቃጠሎና ዘረፋ ተከትሎ ምክር ቤቱ ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ አቋቁሟል።
ከችግሩ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ፣ የችግሩን መንስኤና የጉዳት መጠኑን የሚያጣራ ኮሚቴ ወደ ስፍራው እንደሚልክ ምክር ቤቱ አስታውቋል።
ይህ ድርጊት በሀገራችንም ሆነ በክልሉ ያለውን አብሮነትና የመተሳሰብ ባህል የሚንድ ተግባር እና አለም አቀፍዊ ህግን የሚጻረር በመሆኑ አወግዛለሁ ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ድርጊቱን በማውገዝና በቦታው በመገኘት የደረሰውን ጉዳት በመመልከት ማህበረሰቡን በማጽናናት ላሳዩት አብሮነት አመስግኖ በቀጣይ መሰል ችግር እንዳይከሰት ሃላፊነታችንን በጋራ እንወጣ ሲል ጥሪውን አስተላልፏል።
የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት ዜጎችን የመጠበቅና አጥፊዎችን ለፍርድ የማቅረብ ሃላፊነታቸውንም እንዲወጡም ነው የጠየቀው።
ሙስሊሙ ማህበረሰብ ድርጊቱን በፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማውገዙም አመስግኗል።