በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶች በውይይት መፍታትን እንደሚያበረታታ ኢጋድ ገለፀ
አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሶስቱ ሀገራት መካካል ያሉ ልዩነቶች በውይይት መፍታትን እንደሚያበረታታ አስታውቋል።
የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፥ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል የሚደረጉ ውይይቶችና ድርድሮች ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
በግድቡ ዙሪያ የሚደረገው ድርድር ዘላቂ መፍትሔ እንዲያመጣ ውይይቶች እና የመፍትሔ ሐሳቦች መቀጠል እንዳለባቸው መክረዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ስጋት የሚፈጥሩ ነገሮች አያስፈልጉትም ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፥ የቀጠናውን ሰላምና መረጋጋት ሊያደፈርሱ ከሚችሉ ጉዳዮች በመቆጠብ ጎረቤት ሀገራት የሚጋሯቸውን የጋራ እሴትና ታሪኮች ማጠናከር ላይ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በዓባይ ወንዝ እኩል ተጠቃሚነት ላይ ከስምምነት ለመድረስ ከተፈለገ ለድርድር መዘጋጀትና መንገዱን ማመቻቸት ለሁሉም አካል ጠቃሚ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ ህብረት መሪነት በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል እየተካሄደ ያለው ድርድር ውጤት እንደሚያመጣም በኢጋድ በኩል ሙሉ እምነት እንዳለም አስታውቅዋል።