Fana: At a Speed of Life!

ለመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተዘጋጀው የታሪክ መማሪያ ሞጁል ላይ ግምገማ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተዘጋጀው የአፍሪካ ቀንድና የኢትዮጵያ ታሪክ መማሪያ ሞጁል ላይ በአዲስ አበባ ግምገማ እየተካሄደ ነው።

በግምገማ መድረኩ ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የታሪክ መምህራን፣ የታሪክ ተመራማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፥ ባለፉት ዓመታት ተማሪዎች የሀገራቸውን ታሪክ መማር እንዳይችሉ እንደ ሀገር በታየው ዳተኝነት ምክንያት ትርክቶች የታሪክን ቦታ ይዘው አለመግባባቶችና ጥርጣሬዎች እንዲያድጉ እድል መፍጠሩን አብራርተዋል።

ታሪክ በአንድ ወቅት በተወሰነ ቦታ ስለተፈፀሙ ጉዳዮች የሚያትት መሆኑን ያስረዱት ሚኒስትር ዲኤታው፥ ከእነዚህ ክስተቶች አስተማሪውን ታሪክ ነቅሶ በማውጣት ዛሬን በአግባቡ መረዳትና ቀጣዩን ለመትለም መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

በያዝነውና በጨበጥነው እውቀት ሌላ ቁስል መፍጠር ወይም ቁስሉን በመነካካት ሌላ ቁርሾ ማስነሳት ዘመኑ የደረሰበትን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ድርጊት መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ስለሆነም የትናንቱን ጉዳት በእርቅና በይቅርታ ተሻግሮ ወደ ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ ማፋጠን ይገባል ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው።

ቅራኔና ጥርጣሬ በቀላሉ የሚፈጥሩ ይዘቶች የሞጁሉ አካል አይሆንም ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፥ ለግምገማ የተዘጋጁ የታሪክ ምሁራን ለኢትዮጵያ አንድነት እና ለህዝቦች አብሮነት አምድ የሆኑት እሴቶች ተገቢውን ክብር በሚሰጥ ደረጃና ቋንቋ መፃፋቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ምሁራኑ በዩኒቨርሲቲዎቻቸው ተወያይተው ያመጧቸው አስተያየቶች ዙሪያ እስከ ነገ ድረስ ውይይት ከተካሄደ በኋላ የፊታችን ቅዳሜ በጋራ የተስማሙበትን ሞጁል ያጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.