ከደምበል (ዝዋይ) ሃይቅና ከቆቃ ሃይል ማመንጫ ግድብ ላይ ለ30 ቀናት የሚቆይ እንቦጭን የማስወገድ ዘመቻ ነገ ይጀመራል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ከደምበል (ዝዋይ) ሃይቅና ከቆቃ ሃይል ማመንጫ ግድብ ላይ ለ30 የስራ ቀናት የሚቆይ እንቦጭን የማስወገድ ዘመቻ ነገ እንደሚጀመር ተገለጸ፡፡
ዘመቻው በጣና ሃይቅ ላይ ከጥቅምት 9 እስከ ህዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ሲካሄድ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ በተባበረ የሰው ሃይል እንቦጭን የማስወገድ ዘመቻ ከጣና ሃይቅ ላይ 85 በመቶ የሚሆነውን ማንሳት ተችሏል፡፡
ከዚህ የተገኘው ውጤትና ተሞክሮ ወደ ሌሎች ተፋሰሶች መስፋት ያለበት በመሆኑ በደምበል ሃይቅና በቆቃ ሃይል ማመንጫ ግድብ ላይ እንዲጀመር መወሰኑ ተገልጿል፡፡
በመሆኑም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን እና ከኦሮሚያ ክልል መዋቅር ጋር በመሆን ከጣና ሀይቅ አረም የማስወገድ ዘመቻ ስራ የተገኘውን ልምድ በመቀመር አረሙን በሰው ጉልበት ለማስወገድ በሞዴል ደረጃ በ980 ሄክታር ላይ በተመረጡ አዋሳኝ ቀበሌዎች ላይ የዘመቻ ስራው ይሰራል ተብሏል፡፡
በደምበል ሀይቅ ዙሪያ በአጠቃላይ 31 ቀበሌዎች 1 ሺህ 126 ነጥብ 69 ሄክታር የሚያክለው የውሃ አካል በእንቦጭ ተወሯል፡፡
የአረሙም ስርጭት በቆቃ ግድብ ዙሪያ በሚገኙ ወረዳዎች በቦራ፣ በሎሜ፣ በዶዶታ በሚገኙ በ13 ቀበሌዎች 2 ሺህ 842 ሄክታር ላይ አረሙ ተንሰራፍቷል፡፡
ሁለቱን ሃይቆች ከአረሙ ነጻ የማውጣት ዘመቻው ለሚቀጥሉት 30 ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ነገ በይፋ በባቱ ከተማ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተከናውኖ ስራው የሚቀጥል መሆኑን ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡