Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ አንድ ግለሰብን በማገት 30 ሚሊየን ብር ከቤተሰብ ለመቀበል ሲያስገድዱ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ 7 የምርመራ ቀናትን ፈቀደ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 15 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤት አራዳ ምድብ አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ ጉዳያቸው የታየላቸው ተጠርጣሪዎች ሙሴ ክብረአብ የተባለን ግለሰብ በማገት 30 ሚሊየን ብር ለመቀበል ሲያስገድዱ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ተጠርጣሪ ያሬድ ኦሊቃ እና ፍቃዱ እዩኤል ከእገታ በተጨማሪ የፖሊስና የመከላከያ የደንብ ልብስን በመጠቀም እና የጦር መሳሪያ በመያዝ በማታለልና በህገወጥ የሰዎች ዝውውርም ተሳትፎ እንዳላቸው መርማሪ ፖሊስ ገልጿል፡፡
የተገለፁትን ጨምሮ 5 ተጠርጣሪዎች ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን መርማሪ ፖሊስ 3ኛ ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢወጡ አልቃወምም ማለቱን ተከትሎ ችሎቱ በ5 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ፈቅዷል፡፡
ነገር ግን የ1ኛ እና 2ኛ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ተመልክቷል::
ፖሊስም በተሰጠው ጊዜ ውስጥ የስድስት ሰዎችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ የአንድ ተጠርጣሪን የተከሳሽነት ቃል መቀበሉን እና በምስክር የማስመረጥ ስራ መስራቱን ለችሎት አስረድቷል፡፡
ታጋቹ ግለሰብ በጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት ጉዳትም ቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልገው ፖሊስ በማብራራት የህክምና ማስረጃ ለማምጣት መጠየቁን ገልጿል፡፡
1ኛ እና 2ኛ ተጠርጣሪዎች ለእገታ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ተሸከርካሪዎች እና የሞባይል ልውውጥ መልዕክቶቻቸውን ማስረጃ ማምጣት ይቀረኛል ያለ ሲሆን፤ ተጠርጣሪዎቹ ለዕገታ የጦር መሳሪያና የፀጥታ አካላትን አልባሳት በመጠቀም ደህንነት እና ኮማንደር ነን እያሉ ሲያታልሉ እንደነበር በባለፈው ቀጠሮ ፖሊስ መግለፁ አይዘነጋም፡፡
መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ላይ በርካታ የምርመራ ስራ መስራቱን ገልፆ ተጨማሪ 14 ቀን ጠይቋል፡፡
የ1ኛ ተጠርጣሪ ጠበቃ ደንበኛው ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት እንደሌለው በመግለፅ ዋስትና ስለማያስከለክል ዋስትና እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
2ኛ ተጠርጣሪ በበኩሉ ምርመራው ተገቢነት የለውም ሲል ተቃውሞ ተከራክሯል፡፡
ችሎቱ ግራ ቀኙን አይቶ ለመርማሪ ፖሊስ 7 ተጨማሪ ቀናትን ፈቅዷል፡፡
በአዱኛ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.