ባዕድ ነገር ከማር እና ከቅቤ ጋር ቀላቅለው የሚሸጡ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 25 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ባዕድ ነገር ከማር፣ ከቅቤ እና ከጠጅ ጋር ቀላቅለው የሚሸጡ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ማር ባለ 50 ኪሎ ግራም 1 ሺህ 196 ማዳበሪያ፣ 80 ባልዲ ማር፣ ለጠጅ የተዘጋጀ 10 በርሜል ማር፣ አንድ ደርዘን ወይም 10 ፍሬ ነጭ ቀለም ያለው የማር መቀመሚያ፣ ግማሽ ማዳበሪ ጨው፣ ጨው መሰል የውሃ ማጣሪያ ባዕድ ነገር እና 45 ኪሎ ግራም ስኳር ተይዟል።
በተጨማሪም 228 ማዳበሪያ ባለ 50 ኪሎ ግራም ቅቤ፣ አራት ካርቶን ቅቤ፣ 96 ባልዲ የቅቤ መቀመሚያ፣ 35 ባልዲ ቦቼ የሚረጋ ዘይት መያዙን ከፌደራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ባዕድ ነገሩን ከቅቤና ከማር ጋር ቀምመው የሚሸጡ 72 ተጠርጣሪዎች የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቡድን እና የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ባካሄዱት ዘመቻ በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ሰበታን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፥ ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል ተብሏል።
ኮሚሽኑ ህብረተሰቡ ለበዓል በሚሸምትበት ወቅት ጥንቃቄ እንዲያደርግም ጥሪውን አቅርቧል።