ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ በደቡብ አፍሪካ ለሚያደርጉት ጉብኝት ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በደቡብ አፍሪካ ለሚያደርጉት ጉብኝት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን በፕሬቶሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የፊታችን ጥር 2 እና 3 ቀን 2012 በሀገሪቱ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይታወቃል።
በዚህ ጉብኝት ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል በዳያስፖራና የዜጋ ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮሩ ስራዎች መሆናቸው ተጠቁሟል።
በዚህ መሰረት ጥር 3 ቀን 2012 በኢምፔሪያል ዋንደረርስ ክሪኬት ስታዲየም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የዳያስፖራ መድረክ እንደሚካሄድ ነው የሚጠበቀው።
ይህንን ስራ በተሳካ ሁኔታ ለመምራት የተቋቋሙ የሚሲዮኑና የማህበረሰቡ የጋራ ኮሚቴዎችም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በተገኙበት የስራ አፈጻጸም ግምገማ አካሂደዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያዊያንን መብትና ክብርን ማስጠበቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አካል ሲደረግ የመጀመሪያው ጊዜ መሆኑን በመግለፅ ይህንን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ትልቁ የዳያስፖራ መድረክ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የተካሄደው ውይይት ቀሪ የኮሚቴዎቹን ሰራዎች ገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት አጠቃላይ የቅድመ-ዝግጅቱ ሁኔታ ያለበትን ሁኔታ አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም አብራርተዋል።
የሃብት ማሰባሰብ፣ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን፣ የቅስቀሳና ሌሎች ኮሚቴዎች የስራ አፈጻጸም በዝርዝር የታየ ሲሆን፥ አጠቃላይ ስራው በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መገለፁን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።