የብልጽግና ፓርቲ መመስረት ክልሉ ሀብቱን በአግባቡ እንዲጠቀም አስችሏል-የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ
አዲስ አበባ ፣ጥር 4 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለመተከል ዞን ከፍተኛና እና መካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድር ÷ ክልሉ በተለይ ከአሁን በፊት በነበረው መንግስት በራሱ አመራር ሳይሆን በእንደራሴዎች ተጽዕኖ ወድቆ እንደነበር ገልጸው በሀብቱም ዜጎች ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ተናግረዋል።
አመራሩ የብልጽግናን አስተሳስብ በአግባቡ በመረዳትና በህብረተሰቡ ላይ ለውጡን በማይፈልጉ ሃይሎች የሚነዛውን የተሳሳተ አጀንዳ በመቅረፍ የህዝቡን አድንነት መመለስ እንደሚገባ አቶ ይስሃቅ ገልጸዋል።
በብልጽግና መርህ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሄረሰቦችን አቃፊ እንጅ አግላይ አለመሆኑን ጠቅሰው÷ የህዝብ ይሁንታን ያገኘ እና ለሁሉም ህዝቦች እኩል አመለካከት ያለው አካል እንዲያስተዳደር የሚያስችል ፓርቲ እንደሆነ ተናግረዋል።
በባለፉት ዓመታት በተጽኖ በኢንቨስትመንት ስም የክልሉን መሬት ይዘው ያላለሙ 480 ባለሃብቶች የተነጠቁ እንደሆነ እና በክልሉ ውስጥ ያሉ ስራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ስራ የማስገባቱ ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የብልጽግና ፓርቲ ጽንሰ ሃሳብ ከፖለቲካ፣ከኢኮኖሚ፣ከዲሞክራሲና ከመሰረታዊ መብቶች አኳያ ያለውን አንድምታ ለአመራሩ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ሰጥተዋል።
የብልጽግና ህዝባዊ መሰረት ሁሉን አቀፍ እንደሆነ ገልጸው÷ ሁሉንም ህዝቦች በእኩልነት፣በአንድነትና በፍትሃዊነት በመምራት በዞኑ የተከሰተውን ችግር መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።
የስልጠናው ዋና ዓላማ በአሁኑ ወቅት በመተከል ዞን የተከሰተውን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት አንድ አይነት አመለካከት ያለው የብልጽግና አመራር ለመፍጠር እንደሆነም ተገልጿል።
በመድረኩ እንደተገለጸው የጎራ መደበላለቅ፣የአስተሳሰብ ኋላቀርነት እና ሁሉንም ህዝብ በእኩልነት ያለመምራት በመተከል ዞን ለተከሰተው ችግር መንስኤ እንደሆኑም ተጠቁሟል።
በሚቀጥሉት 15 ቀናት ተዘግተው የነበሩ መሰረታዊ ተቋማትን መክፈት፣ለመንግሥት ሰራተኞች እና ለህብረተሰቡ ተረጋግቶ መደበኛ ስራውን እንዲያከናውን በስነ መግባር የታገዘ አመራር መስጥት፣የተፈናቀሉ ዜጎችን መረጃ ማጠናከርና ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ፣መደበኛ ስራዎችን ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በማቀናጀት መስራት የወደፊት የስራ አቅጣጫዎች ሆነው መቀመጣቸውን ከመተከል ዞን ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!