Fana: At a Speed of Life!

ዳያስፖራው ድጋፍና አብሮነቱን ለማሳየት ለገበታ ለሃገር 27 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ድጋፍና አብሮነታቸውን ለማሳየት ለገበታ ለሃገር ፕሮጀክት 27 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል በቀጣይ ሳምንት በሚዘጋጀው የእራት መርሃ ግብር ላይ እንዲሳተፉ እጣ የወጣላቸው 11 የዳያስፖራ አባላት ዝርዝርም ይፋ ሆኗል።
በብሔራዊ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ የውጭ ድጋፍ አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች ለሚገነቡት ፕሮጀክቶች ዳያስፖራው በተለያየ መልኩ ድጋፍ እያደረገ ነው።
“ለኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪ ፕሮጀክቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጥሪ መሰረት ዳያስፖራው ድጋፉንና አብሮነቱን እያሳየ ነው” ብለዋል።
በዚህ አመት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመላው ዓለም ከሚገኘው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ለገበታ ለሃገር ፕሮጀክት 50 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን አብራርተዋል።
በሁለተኛው ሩብ አመት ለመሰብሰብ ከታቀደው 15 ሚሊየን ብር 27 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትር ዲኤታዋ ገለጻ ድጋፉን ኢትዮጵያ ውስጥ በተከፈተው የባንክ ሂሳብ ቁጥር፣ በሚሲዮኖችና ዳያስፖራው በግል፣ በቡድን፣ በማህበርና በድርጅት ስም ለፕሮጀክቱ ገቢ አድርጓል።
በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ልማት ለመሳተፍ እያሳዩ ያለውን ተነሳሽነት በመጠቀም በቀሪው ጊዜ ተጨማሪ ገቢ ለመሰብሰብ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በቀጣይ ሳምንት በሚካሄደው የገበታ ለሃገር የእራት መርሃ ግብር ላይ አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል ከአፍሪካ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅና ከሌሎች አካባቢዎች እጣ የወጣላቸው 11 የዳያስፖራ አባላት ተሳታፊ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።
እጣ የወጣላቸው የዳያስፖራ አባላት አቶ የማነ በርሔ ወልደስላሴ፣ አቶ ዳንኤል በርሔ ወልደስላሴና አቶ መርሃዊ መስፍን ተስፋስላሴ ከአፍሪካ ደቡብ ሱዳን ናቸው።
በተመሳሳይ አቪያ ሆልዲንግስ ኮርፖሬሽን፣ ሶፊያ ዘውዱ አበራና አቶ አልታየወርቅ ብርሃነ ስላሴ ከሰሜን አሜሪካ ዩናይትድስቴትስ እጣ የወጣላቸው ናቸው።
ከአውሮፓ ጄኔቫ ደግሞ አቶ ረሻድ ከማል ጎበና እንዲሁም ከብራሰልስ ወይዘሮ ተዘራሽ ሽፈራው፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እስራኤል አቶ ሙሉጌታ ገብሩ ይሳተፋሉ።
ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች አቶ አብዱልናስር ሃሮና ሻለቃ ጥሩነህ አላምረው እጣ ከወጣላቸው 11 የዳያስፖራ አባላት ውስጥ በመሆናቸው በመርሃ ግብሩ ይሳተፋሉ።
ዳያስፖራው ለህዳሴ ግድብ፣ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝና ለተለያዩ ሰብአዊ እርዳታና ኢትዮጵያን ለማልማት መንግስት በሚቀርጻቸው ፕሮጀክቶች ዳያስፖራው በእውቀት፣ በገንዘብና በሌሎች ተነሳሽነቱ መጨመሩን ገልጸዋል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.