የአፈር ማዳበሪያን ወደ ሀገር ውስጥ ማጓጓዝ የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ለ2012 ዓ.ም ለግብርና ግብዓት የሚሆን የአፈር ማዳበሪያን ወደ ሀገር ውስጥ ማጓጓዝ የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለጸ።
ድርጅቱ ለተያዘው በጀት ዓመት ለግብርና ግብዓት የሚሆን የአፈር ማዳበሪያን ከውጭ ሀገራት ወደ ጅቡቲ ወደብ የማጓጓዝ ስራ መጀመሩን አስታውቋል።
በዚህ መሰረት የአፈር ማዳበሪያ የጫነች የመጀመሪያዋ መርከብ በትናንትናው ዕለት ጅቡቲ ወደብ መድረሷ ነው የተገለጸው።
መርከቧ ከግብፅ አዲባይ ወደብ የጫነችውን የመጀመሪያ 50 ሺህ ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ በጅቡቲ ወደብ የማራገፍ ስራ ጀምራለች ተብሏል።
በቀጣዩ ሳምንትም ከሞሮኮ ጆርፍ ላስፈር ወደብ የአፈር ማዳበሪያ የጫኑ ሁለት መርከቦች ጅቡቲ ወደብ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅትም ጭነቱን በተቀላጠፈ ሁኔታ ወደ ሀገር ውስጥ ለማጓጓዝ የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል።