የትራፊክ ክፍያ አገልግሎት ከሰኞ ጀምሮ በከተማዋ ውስጥ ባሉ አምስት ባንኮች መሠጠት ይጀምራል
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ክፍያ አገልግሎት ከሰኞ ጀምሮ በከተማዋ ውስጥ ባሉ አምስት ባንኮች መሰጠት እንደሚጀምር አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የትራፊክ ክፍያን በዘመናዊ መንገድ መቀየር በሚቻልበት አግባብ ላይ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል።
የትራፊክ ክፍያ አገልግሎት የ”ለሁሉ” አገልግሎት ከተቋረጠ በኋላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ብቻ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ይህም አሽከርካሪዎች እንዲጉላሉ እና ረዥም ወረፋ እንዲጠብቁ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል።
ይህን አሰራር በዘመናዊ መንገድ ለመቀየርም የከተማ አስተዳደሩ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።
አሽከርካሪዎች የትራፊክ ክፍያዎችን በአቅራቢያቸው ባሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ፣ የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የአቢሲኒያ ባንክ እና የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች በመሄድ ክፍያ መፀጸም ይችላሉ ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም የትራፊክ ቅጣት መክፈል የሚችሉበት አዲስ አሰራር በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመዘርጋት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየተሰራ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ሌሎች ዘመናዊ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ክፍያዎችን መፈጸም በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ እየተሰራ መሆኑን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።