በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለጃዋር መሀመድ የሞባይል ሲም ካርዶችን ሊያቀብል ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል የተባለው ግለሰብ ዋስትና ተፈቀደለት
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለጃዋር መሀመድ 4 የሞባይል ሲም ካርድ ሊያቀብል ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል የተባለው ግለሰብ ዋስትና ተፈቀደለት፡፡
ተጠርጣሪ ሀምዛ ጀማል አንድ በኦ ኤም ኤን ድርጅት ስም እና 3 በግለሰብ ስም የወጡ ሲም ካርዶችን ለጃዋር መሀመድ ሊያቀብል ሲል በማረሚያ ቤቱ የጥበቃ አባላት በቁጥጥር ስር ውሏል ተብሎ ከአንድ ወር በላይ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ሲደረግበትና ለአራት ጊዜ ፍርድቤት ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
በምርመራው መርማሪ ፖሊስ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ምስክር ቃል መቀበሉን ከኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርዱ በማን ሰም ስለመውጣቱ ማስረጃ መሰብሰቡን ገልጾ ነበር፡፡
የምርመራ መዝገቡን ዐቃቤ ህግ እየተመለከተው መሆኑን እና ተጨማሪ ምስክር ለመቀበል ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ጠይቆ የነበረ ሲሆን የተጠርጣሪ ጠበቃ በቂ ጊዜ ተሰጥቷል ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ አግባብ አይደለም ሲል ተቃውሞ ተከራክሮ ነበር፡፡
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት መርማሪ ያቀረበው የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት አሳማኝ ምክንያት አይደለም ሲል አልተቀበለውም፡፡
እስካሁን በምርመራ ቀናት የተከናወኑ ስራዎች በቂ ናቸው ሲል ተጠርጣሪው የ30 ሺህ ብር ዋስ አስይዞ ከማቆያ እንዲፈታ ዋስትና ፈቅዷል፡፡
በታሪክ አዱኛ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!