አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አስታወቁ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ገንቢ በሆነ መልኩ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አስታወቁ፡፡
አምባሳደር ታዬ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በተለይ በትግራይ ክልል እየተከናወኑ ስለሚገኙ ተግባራት በጻፉት ደብዳቤ አብራርተዋል፡፡
በደብዳቤያቸውም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መንግስት በትግራይ ክልል እያደረገ ላለው የሰብአዊ ድጋፍና መልሶ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል፡፡
አምባሳደር ታዬ በደብዳቤያቸው ህወሓት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውሰው፥ ይህን መሰሉ ወንጀል በሌሎች ሃገራት ያልታየ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም መንግስት ህግና ስርአትን ለማስከበር አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሂደትም የዜጎች መፈናቀልና የመሰረተ ልማት ውድመት መከሰቱን ጠቁመው፥ መደበኛ ህይወት መስተጓጎሉንና በተለይም በትግራይ ክልል የምግብ እጥረት ማጋጠሙን አስታውቀዋል፡፡
መንግስትም ከአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ አንጻር ለሰብአዊ ድጋፍ ቅድሚያ መስጠቱን ያነሱት አምባሳደሩ፥ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላትም ከሃገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም መንግስት ከተመድ ጋር የሰብአዊ ድጋፍ ትብብር ስምምነት መድረሱን በመጥቀስም፥ ይህም የረድኤት ድርጅቶች በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርሱ አስችሏቸዋልም ነው ያሉት፡፡
በሰብአዊ ድጋፍ ሂደቱ የተመድ ተቋማትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሰጡት ምላሽ መንግስት ያለውን አድናቆትም ገልጸዋል፡፡
ከሰብአዊ መብት ጋር በተያያዘም መንግስትና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፥ አሉ የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ የሚያደርጉትን ምርመራ እንደሚቀጥሉና ግኝታቸውን ይፋ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ሂደት መንግስት ለሚደረግለት ድጋፍና በትብብር ለመስራት ዝግጁ ነው ያሉት አምባሳደር ታዬ፥ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብትን ለማስከበር እና የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ቁርጠኛ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ አሉ ከተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ ተሳትፈተዋል የተባሉ አካላትን ለህግ ታቀርባለችም ነው ያሉት፡፡
በትግራይ ክልል ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞም መንግስት አስፈላጊውን መረጃ ለመስጠትና ለማድረስ ዝግጁ መሆኑ ገልጸው፥ ከዚህ ጋር ተያይዞም መገናኛ ብዙሃን ያለውን ሁኔታ እንዲታዘቡና እንዲዘግቡ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱንም አንስተዋል፡፡
በዚህ ሂደት በርካታ መገናኛ ብዙሃን በክልሉ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በማውሳትም፥ መገናኛ ብዙሃኑ ክልሉን በተመለከተ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየወጡ ላሉ የተዛቡ መረጃዎች ምላሽ ይሰጣሉ ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!