Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት ተቀራርበው መስራት ይገባቸዋል-የዩጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር 

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 3 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  በዩጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለምጸሀይ መሰረት ከዩጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ሳም ኩቴሳ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮችና በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱም ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ የቆየ እና ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ግንኙነቱም በልዩ ልዩ መስክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን በሁለቱም በኩል ተገልጿል።

በዚሁ ወቅት አምባሳደር አለምፀሀይ በተለይም መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለውን መጠነ ሰፊ  የመልሶ ግንባታ እና ሰብዓዊ እርዳታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስትም የትግራይ ክልልን  ለአለምአቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎች እና ለአለምአቀፍ ሚዲያዎች ያለ ገደብ ክፍት ማድረጉን አስረድተዋል።

አያይዘውም የአለምአቀፍ ማህበረሰቡና እርዳታ ሰጪዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡን እና መሬት ላይ ያለው ሀቅና በተወሰኑ የሚዲያ አካላት የሚነዛው የተሳሳተ ትርክት የተለያየ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

አምባሳደሯ አያይዘውም ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት በሀይል እንደያዘችና ይህም የሁለቱን ህዝቦች የቆየ ግንኙነት እንደማይወክል ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የተፈጠረውን የድንበር ውዝግብ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት  እያደረገች ያለውን ጥረትም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ኢትዮጵያ ውይይት ከመጀመሩ በፊት ሱዳን የያዘችውን መሬት በአስቸኳይ ለቃ እንድትወጣ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጧን ገልጸዋል።

ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን መፍትሄ በሚል ሶስቱ ሀገራት ጉዳዮን በአፍሪካ ህብረት አጋዥነት መፍታት የሚያስችል አቅም አለ ብላ እንደምታምንአምባሳደሯ ገልፀዋል፡፡

የዩጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ሳም ኩቴሳ በበኩላቸው÷ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት ተቀራርበው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

አያይዘውም ሁለቱ አገራት የድንበር ጉዳዩን በተመለከተ በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለቀጠናው ሰላም አስተዋፅኦ ማድረግ  እንደሚገባቸው ጠቁመው ÷የናይል ወንዝን በተፋሰሱ ሀገራት ያለው ችግር የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት እንጂ የውሃ እጥረት አለመሆኑን እንዲሁም ሊከሰት የሚችል የውሃ እጥረትንም አስቀድሞ ለመከላከል ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በመወያየት የውሃ ሀብት ልማት ስራዎች ላይ በጋራ መስራት እንደሚገባቸው  መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.