Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን ምሁራን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ የሚቃወም ደብዳቤ ለፀጥታው ምክር ቤት አስገቡ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን አሜሪካ እና የተወሰኑ ምዕራባውያን ሃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እያደረጉት ያለውን ጥረት የሚቃወም ደብዳቤ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ ለአውሮፓ ህብረትና ለሩሲያ ማስገባታቸውን ገለፁ፡፡
በጀርመን በርሊን የሚኖሩት እና የምጣኔ ሃብት እና የፕሮጀክት አስተዳደር ባለሙያ  ዶክተር ፀጋዬ ደግነህን ጨምሮ ሌሎች ከአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የተውጣጡ 33 ምሁራን ለተቋሞቹ የተቃውሞ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡
ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ እና በሩሲያ የአፍሪካ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ዘነበ ክንፉ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግን እንቅስቃሴ እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ፀጋዬ የአውሮፓ ህብረት የህዝብ እንደራሴዎች አሁን ላይ በተሳሳተ መረጃ እና የእነርሱን ጥቅም ብቻ በማስቀደም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እየሞከሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ይህ አይነቱ አካሄድ ህብረቱን አደጋ ላይ እንደሚጥልና በተለይም በዲፕሎማሲው ጉዞ በቀጣይ የአጋርነት ጉዳይ ላይ ጥያቄ ሊያስነሳበት ስለሚችል ቆም ብሎ እንዲያጤነው አሳስበናል ብለዋል፡፡
እንዲሁም በደብዳቤው የፅንፈኛው የህወሓት ቡድን የትናንት የጥፋት ድርጊት እና የዛሬ አሳሳች መረጃዎችን በጥንቃቄ አካተናል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል ዶክተር ፀጋዬ በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የነቃ ተሳትፎ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፈጣን መረጃ ለማድረስ መትጋት ይገባዋል ብለዋል፡፡
በሩሲያ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ትውልደ ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር እና የአፍሪካ ዳያስፖራዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ዘነበ ክንፉ በበኩላቸው ሰሞነኛው አካሄድ በሩሲያ የአፍሪካ ዳያስፖራዎችን ክፉኛ አስቆጥቷል ነው ያሉት።
በሩሲያ እና በቤላሩስ እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በመሰባሰብ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስቀድም አንድ አቋም መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም በመካከላችን ልዩነት ቢኖር እንኳን በኢትዮጵያ ጉዳይ በአንድነት ከመስራት የሚያግደን ነገር እንደሌለ ተስማምተናል ብለዋል፡፡
በስላባት ማናዬ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.