በባህርዳር ከተማ ፈለገህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ክትባት መሰጠት ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ፈለገህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ክትባት በዛሬው ዕለት መሰጠት ተጀምሯል፡፡
በክትባቱ ወቅት የክልሉ የክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገርና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በክትባቱ የተገኙት የክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ ፣ የጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ና ሌሎች አመራሮች ና የጤና ባለሙያዎች ክትባቱን ወስደዋል፡፡
በሀገር አቀፍ በተሰጠው ኮታ መሰረት 108 ሺህ ዶዝ ክትባት ለአማራ ክልል መሰጠቱን የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ገልፀዋል፡፡
በአማራ ክልል 251 ሺህ 597 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተመረምረው 7 ሺህ 392 ቫይረሱ ሲገኝባቸው 6 ሺህ 826 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል፡፡
በተጨማሪም እስካሁን 140 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡
በናትናኤል ጥጋቡ