Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ፡፡

ውይይታቸው በዋናነት በሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል፡፡

ከደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሲዮክ ሂ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ደቡብ ኮሪያ ላደረገችው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ የምትከተለውን የልማት ሞዴል ኢትዮጵያ እንደምታደንቅም በዚህ ወቅት ገልጸውላቸዋል፡፡

አምባሳደር ካንግ ሲዮክሂ በበኩላቸው በኮሪያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከደቡብ ኮሪያ ጎን በመቆም ያደረጉትን አስተዋጽኦ አስታውሰው፥ በሃገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት በደም የተሳሰረ ታሪካዊ ግንኙነት መሆኑን አውስተዋል፡፡

ግንኙነቱን ከሁለትዮሽ ትብብር ባሻገር በቴክኖሎጂ ሽግግር እና የልማት ፕሮጀክቶች ትብብር የበለጠ ማጠናከር ይገባልም ብለዋል፡፡

በተያያዘም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ጋር ባደረጉት ውይይት በሃገራቱ መካከል በመሰረተ ልማት፣ በትምህርት እንዲሁም በልምድ ልውውጥ ያላቸውን ትብብር አድንቀዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የጃፓን መንግስት በጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ ለሚያደርገው የልማት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በውይይታቸው ወቅት በትግራይ ክልል እየተደረገ ስላለው የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትና ሌሎች ስራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.