የኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ ቡርጂ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች የጋራ ዕርቀ ሰላም ጉባኤ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ ቡርጂ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች የጋራ ዕርቀ ሰላም ጉባኤ በዛሬው ዕለት በሰገን ከተማ ተካሂዷል።
በዕርቀ ሰላም ጉባኤው የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ፣ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኅላፊዎችና የሐይማኖት አባቶች እንዲሁም የጎሳ መሪዎች ተገኝተዋል።
ኮንሶ በአካባቢ ጥበቃ እና ቅርስ ምሳሌ የሆነ ማህበረሰብ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለያዩ የሰብል ምርቶች የሚታወቀው አካባቢው በተፈጠረው ግጭት እጅግ ተጎድቶ ቆይቷል ብለዋል።
አካባቢው መገለጫው መልካም ነገሮች እንደመሆናቸው ወደ ሰላም ለመመለስ የዕርቅ ሂደቱ እንዲሳካ በየደረጃው ኃላፊነት ወስደው የሰሩ አካላትንም አመስግነዋል።
የሚወድመው የእኛው ንብረት የሚፈናቀለው የእኛው ህዝብ እንጂ ሌላ አይደለም ያሉ ሲሆን፤ እከመጨረሻው ከችግሩ የምንላቀቅበትን ዕርቀ ሰላም ሊሆን ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመደማመጥ በመነጋገር ችግሮችን መፍታት እየተቻለ ጥቂት ግለሰቦች በሚያሰራጩት የጥላቻ ስብከት መፈጠር ያልነበረበት ውድመት የተከሰተ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ ይህ ሊደገም አይገባም ብለዋል።
የትኛውም አይነት ጥያቄ አለኝ ለሚል ሰው መንግስት በሩ ክፍት ነው በግጭት የሚፈታ ግን አይኖርም ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት መስራት ይገባል ብለዋል።
መጪው ጊዜ የአብሮነት የወንድማማችነት እና ብልፅግናችንን የምናረጋግጥበት ነው ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየው በበኩላቸው፤ ኮንሶ ቡርጂ አማሮና ደራሼ ለዘመናት ተጋምደው በደም ተሳስረው በአብሮነት የሚኖሩ እንደመሆናቸው በግለሰቦች እና በቡድን ፍላጎት ምክንያት የህዝቡ አብሮነት አይናድም ብለዋል።
አስተዳዳሪው ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም ዘብ እንዲቆም ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የተፈጠርውን ችግር ተሻግረን በአንድነት እና በሰላም የብልፅግና ጉዞአችን ላይ እናተኩራለንም ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የፀጥታና ኃላፊ ቢሮ አቶ አለማየው ባውዴ በዕርቀ ሰላም ጉባኤው ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በላይ የጥፋት አጀንዳ አንግበው በሚንቀሳቀሱ አካላት በአካባቢው ከፍተኛ ጉዳት የተከሰተ ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን በተጀመረው የዕርቀ ሰላም ጉባኤ ጥላቻና መገፋፋት ተቀብረዋል ብለዋል።
ለዕርቀ ሰላሙ መሳካት አስተዋፅኦ ላረጉ አካላት ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።
የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የጎሳ መሪዎችም በዋጋ የማይተመነውን ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም በህብረት እና በወንድማማችነት ሊቆም ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመለሰ ምትኩ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!