የስድስት ከተሞች የመረጃ አስተዳደር በቅርቡ ስራ ይጀምራል
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የስድስት ከተሞች የመረጃ አስተዳደር በቅርቡ ስራ ይጀምራል፡፡
የመረጃ አስተዳደሩ ከተሞች ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የሚሰሩትን ስራ ህዝብ እንዲያውቅላቸው፣ የሚሰጡት አገልግሎት እንዲተዋወቅ፣ ከውጭ የሚመጡ ሰዎች የተሟላ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል።
በዚህም አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ ሃዋሳ፣ አዳማ እና አርባምንጭ ከተሞች የከተማ መረጃ አስተዳደር እየለማላቸው ሲሆን÷ ራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ ለባለሙያዎቻቸው በስራ አመራር ኢንስቲቲዩት ስልጠና እየተሰጠ ይገኛልም ነው የተባለው።
ስልጠናው ከተሞቹ የመረጃ አስተዳደሩን እንዲያስተዳድሩ፣ መረጃ እንዲያከማቹ፣ አዳዲስ ማሻሻያዎችን እንዲጨምሩ፣ አጠቃቀሙን እንዲያውቁ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚያስችላቸው መሆኑ ተመላክቷል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አብዮት ባዩ ÷የከተማ መረጃ አስተዳደር ዜጎች በቂ መረጃ እንዲያገኙና ከተሞች እድገታቸው እንዲፋጠን ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
በቀጣይ ሌሎች ከተሞችም የከተማ የመረጃ አስተዳደር እንዲኖራቸው እንደሚሰራም አብራርተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየሁለት አመቱ የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ የሚወጣ ሲሆን÷ ይህ ስራም ኢትዮጵያ ያላትን ደረጃ ለማሻሻል የሚሰሩ ስራዎች አካል መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።