ለትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር ድጋፍ ማድረጌን እቀጥላለሁ – የዓለም የምግብ ፕሮግራም
አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ መንግስት ለጀመረው አገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ካትሪን ፊኒ እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ መንግስት የትምህርት ቤት ምግባ መርሃ-ግብር ፖሊሲና ስትራቴጂ በማጽደቅ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚያስመሰግን ነው፡፡
የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር የትምህርት ተሳትፎና የመማር ምጣኔን ከማሻሻል ባሻገር የስርዓተ ጾታን ክፍተት የመሙላት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ምክትል ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረው ብሄራዊ አገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር ከግብ እንዲደርስ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የዓለም የምግብ ፕሮግራም የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ-ግብርን ለማጠናከር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በአጋርነት ሲሰራ መቆየቱንም ካትሪን ፊኒ መጥቀሳቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
በዚህም መንግስትና የዓለም የምግብ ፕሮግራም በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር አማካይነት የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ጨምሮ የምግብ እጥረት ባለባቸው የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን መድረስ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የዓለም የምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ በትምህርት ቤቶች ምገባ መርሃ-ግብር ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በአጋርነት እየተሳተፉ ያሉ ሁሉንም ባለድርሻዎች አመስግነዋል፡፡

ሚኒስትሩ ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም መጠየቃቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!