ኮርፖሬሽኑ ሻንግቼንግ ኩባንያ ጋር በደብረ ብርሀን ኢንዱስትሪያል ፓርክ 3 ሼዶችን ለማከራየት የውል ስምምነት ፈጸመ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሻንግቼንግ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር በደብረብርሀን ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሶስት ሼዶችን ለማከራየት ዛሬ የውል ስምምነት ፈጽሟል፡፡
የሼድ ኪራይ ውሉን ለማካሄድ የሚያስችለውን የውል ስምምነት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ እና የሻንግቼንግ ዋና ስራ አስኪያጅ ካንዲ ተፈራርመዋል፡፡
ሻንግቼንግ በጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ የተሰማራ የቻይና ኩባንያ ሲሆን÷ ከቻይና ውጪ መዋዕለ ንዋዩን ሲያፈስ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ኩባንያው ስራውን በ3 ነጥ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚጀምር ነው የተገለጸው፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ÷ኩባንያው በደብረ ብርሀን ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሶስት ሼዶችን ተከራይቶ ስራ ለመጀመር የውል ስምምነት በመፈፀሙ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው ከስራ ዕድል ፈጠራ ከቴክኖሎጂ ሽግግር እና ከውጪ ምንዛሬ አኳያ የሚያስገኘው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ሻንግቼንግ ስራውን ሲጀምር ከ2 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን÷ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ደግሞ የስራ ዕድል ፈጠራው እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡
ኩባንያው በምርት ሂደት ውስጥ ቲሸርቶችን፣ ጃኬቶችን፣ ሸሚዞችን እና የውስጥ ሱሪዎችን የሚያመርት ይሆናል፡፡
ምርቶቹንም ሙሉ በመሉ ለጃፓን ለአውሮፓ እና ለሰሜን አሜሪካ ሀገራት ገበያ የሚያቀርብ መሆኑን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!