Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ የ2013 በጀት ዓመት የሰራ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 21፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ፣የሴክተር ተቋማት አመራሮች እና የክፍለከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች በተገኙበት የ2013 በጀት ዓመት የሰራ አፈጻጸም ግምገማ በመካሄድ ላይ ነው።

በግምገማው ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪዉ አቶ ጃንጥራር አባይ እንዲሁም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ተገኝተዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ አበይት ዋና ዋና ተግባራት አፈጻጸምና በሂደቱም የታዩ ጠንካራ አፈፃፀሞችና ክፍተቶች ቀርበው ሰፊ ዉይይት እየተካሄደባቸው ይገኛል።

በዋናነትም የከተማዉን ህብረተሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተከናወኑ ሲሆን፥ ህገወጥ የመሬት ወረራ ፣በጋራ መኖሪያ ቤቶች እና በቀበሌ ቤቶች በኩል የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ከመግታት አንጻር አበረታች ዉጤት መመዝገቡ በግምገማዉ ላይ ቀርቧል።

በበጀት ዓመቱ በተለይም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ዉህደትና ቅንጅታዊ ስራዎች ፤ ህብረተሰቡን በማስተባበር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተደረገዉ ድጋፍ፤ የአካባቢ ጽዳት ፣የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፣የአረንጓዴ ልማት እና ሌሎች መርሐግብሮች ላይ የተከናወኑ ተግባራት ለቀጣይ ሰራዎች በጥንካሬ መንደርደሪያ እንደሚሆን ተጠቁሟል።

ተቋማዊ አሰራርን ለማጠናከር እና በህብረተሰቡ በኩል የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለማፍታትም በየደረጃው የሚገኝ አመራር በልዩ ትኩረት መስራት እንዳለበት በግምገማው መመላከቱን ከከተማው ፕረስ ሴክሬታሪ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ዉይይቱ ከሰዓትም የሚቀጥል ሲሆን፥ በቀጣይ አስር ዓመታት የከተማዋን ሁለንተናዊ እድገት እና የነዋሪዎቿን አዳጊ ፍላጎት ባማከለ መልኩ በሚተገበሩና ከተማዋ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞን ማረጋገጥ በሚያስችሉ አበይት ተግባራት ዙሪያ በሚካሄዱ ሰፊ ዉይይቶች ይቀጥላል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.